ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን ጠብቀው ከመከላከያ ጎን በመቆም የአሸባሪው ህወሓትን የጥፋት ሴራ ማክሸፍ አለባቸው

ነሀሴ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን ጠብቀው ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመቆም የአሸባሪው ህወሓትን የጥፋት ሴራ ማክሸፍ እንዳለባቸው የመከላከያ ሰራዊት ሥነ ልቦና ግንባታ ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን ገለጹ፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ የህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ ጉዳት የደረሰባቸውን የመከላከያ ሰራዊት አባላትና ቤተሰቦችን በዘላቂነት ለማቋቋም ያለመ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

መርሃ ግብሩን "አንድነት ይቻላል የበጎ አድራጎት ድርጅት" የተባለ የበጎ አድራጎት ድርጅት ያዘጋጀው ሲሆን ፤ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡

የመከላከያ ሰራዊት ሥነ ልቦና ግንባታ ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ አሸባሪው ህወሓት በመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ጥቃት በማድረስ ታሪክ ይቅር የማይለው የሀገር  ክህደት መፈጸሙን አስታውሰዋል፡፡

የመከላከያ ሰራዊት የዜጎችን ደህንነትና የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ተገዶ በገባበት የህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ አንጸባራቂ ድሎችን አስመዝግቧል ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ የሽብር ቡድኑ መንግስት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ ወደ ጎን በመተው ዳግም ጦርነት ጀምሯል ብለዋል፡፡

በመሆኑም የመከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የህዝቦቿን ደህንነት አስጠብቆ ሰላምን በማረጋገጥ ኃላፊነቱን ይወጣል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብም አሸባሪው የህወሓት ቡድንና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ኢትዮጵያን ለማፍረስ የደገሱትን የጥፋት ሴራ ለማክሸፍ ከመከላከያ ሰራዊቱና ከጸጥታ ኃይሉ ጎን እንዲሰለፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

እንደ "አንድነት ይቻላል የበጎ አድራጎት ድርጅት" አይነት ድርጅቶች ደግሞ ዓላማቸው ከግብ እንዲያደርሱ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍና ክትትል እናደርጋለን ብለዋል፡፡

የአንድነት ይቻላል የበጎ አድራጎት ድርጅት ፕሬዘዳንት ጋዜጠኛ ሰለሞን ኃይለየሱስ፤ የኢትዮጵያን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት ከነ ሙሉ ክብሯ እየጠበቀ ላለው ሰራዊት የሚደረገው ማንኛውም ድጋፍ ቢያንስ እንጂ አይበዛም ብሏል፡፡

ድርጅቱ በሰሜን ኢትዮጵያ በተደረገው የህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ ጉዳት የደረሰባቸው የሰራዊት አባላትንና ቤተሰቦቻቸውን እንዲሁም በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው የማህበረሰብ ክፍሎችን በዘላቂነት ለማቋቋም እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም