በአዲስ አበባ ከተማ የመኖርያ ቤት ኪራይ መጨመርም ይሁን ተከራይን ማስወጣት የሚከለክለው ደንብ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ተራዘመ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ከተማ የመኖርያ ቤት ኪራይ መጨመርም ይሁን ተከራይን ማስወጣት የሚከለክለው ደንብ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ተራዘመ
ነሐሴ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ የመኖርያ ቤት ኪራይ መጨመርም ይሁን ተከራይን ማስወጣት የሚከለክለው ደንብ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት እንዲራዘም ተወስኗል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዜጎች ላይ የሚደርሰውን የኑሮ ጫናን ለመቀነስ በመኖርያ ቤት ተከራዮች ላይ የኪራይ ዋጋ ጭማሪ እና ተከራይን ማስለቀቅን የሚከለክል ደንብ አውጥቶ ተግባራዊ ማድረጉ ይታወቃል፡፡
ይህም ደንብ በተለያየ ጊዜ እየተራዘመ ላለፈው አንድ አመት ተግባራዊ ተደርጎ ቆይቷል፡፡
ስለሆነም የከተማ አስተዳደሩ አሁን ያለውን አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ እና የህብረተሰቡን የኑሮ ጫና ከግምት ባስገባ ወቅቱን በአብሮነትና በመተሳሰብ ለማለፍ ይረዳ ዘንድ ይህ ደንብ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት እንዲራዘም ወስኗል፡፡
በመሆኑም ይህንን ክለከላ በመተላለፍ ተከራዮችን የሚያስወጡ እና የኪራይ ዋጋን የሚጨምሩ አካላት ላይ ማህበረሰቡ በሚከተሉት የስልክ ቁጥሮች ጥቆማውን ለከተማ አስተዳደሩ ማድረስ እንደሚችል የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ አመልክቷል።
አጭር ቁጥር ፡- 9977
የሞባይል ስልኮች 09-00640830 09-00640789
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር