የደቡብ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የ8ኛ ክፍል ፈተና ውጤት ይፋ ሆነ

ነሐሴ 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) የደቡብ ክልል እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ይፋ ሆነ።

ዛሬ ይፋ በተደረገው ውጤት መሰረት ፈተናውን ከወሰዱ ከ257 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከ73 በመቶ በላይ ተማሪዎች ማለፋቸውን ተመላክቷል።

የፈተና ውጤት ይፋ መሆንን አስመልክቶ በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ በሰጡት መግለጫ የክልላዊ ፈተናው ውጤት በሁለቱም ክልሎች የጋራ ውሳኔ የተሰጠ ሲሆን ውሳኔው የትምህርት ጥራት፣ ፍትሀዊነትና ተደራሽነትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

አክለውም በትምህርት ዘመኑ በሁለቱም ክልሎች የተለያዩ ነባራዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ፣ የቀደሙ ውጤቶችን የተመለከተና የሌሎች ክልሎችን ልምድ በመውሰድ የተወሰነ ውጤት መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም በሁለቱ ክልሎች ውሳኔ መሰረት የማለፊያ ነጥብ መቀመጡን ገልጸው፤ ለወንዶች 41፣ ለሴቶች 40 እና ለአይነ ስውራን 39 ሆኖ መወሰኑን አመላክተዋል።

በዚህ መሰረት በ2014 የትምህርት ዘመን በሁለቱም ክልሎች ለፈተና ከተቀመጡ ከ257 ሺህ በላይ ተማሪዎች 187 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎች ወደቀጣይ ክፍል የሚያሳልፋቸውን ውጤት ማስመዝገባቸውን ገልጸዋል።

በውሳኔው መሰረትም ለፈተና ከተቀመጠው አጠቃላይ ተማሪ ቁጥር ሲታይ ከ73 በመቶ በላይ ተማሪዎች አልፈዋል ነው ያሉት።

በተለየ መልኩ ከጸጥታ ጋር በተያያዘ በአሉታዊ ጫና ውስጥ ሆነው የተማሩና ለፈተና የተቀመጡ የደራሼ ልዩ ወረዳ ተማሪዎችን ውጤት በተለየ መልኩ ለማየት መሞከሩን ገልጸዋል።

በዚህም መሰረትም ለወንዶች 39፣ ለሴቶች 38 እና ለአይነ ስውራን 37 ሆኖ መወሰኑን ነው ያስታወቁት ።

የሁለቱ ክልሎች ተማሪዎች ውጤታቸውን ከነገ ጀምሮ መውሰድ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።

የደራሼ ልዩ ወረዳ ተማሪዎች ግን ውጤታቸው በእጅ የሚሰራ በመሆኑ የአንድ ሳምንት ጊዜ ዘግይቶ የሚደርስ በመሆኑ እንዲጠባበቁ አስገንዝበዋል።

የትምህርት ዘመኑ ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎችን ያለፍንበት ነው ያሉት ዶክተር ዲላሞ በፈተናው የማለፍ ዕድል ያገኙ ተማሪዎች በሚቀጥለው ክፍል ተፎካካሪ ለመሆን  ቅድመ ዝግጅት ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም