ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከነበረበት ኪሳራ ወጥቶ ውጤታማ በመሆኑ የሚደነቅና በምሳሌነት የሚወሰድ ነው-የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ

ነሐሴ 19 ቀን 2014 (ኢዜአ)የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከነበረበት ኪሳራ ወጥቶ ውጤታማ በመሆኑ የሚደነቅና በምሳሌነት የሚወሰድ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ተናገሩ።

የመንግስት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር የኢትዮጵያ ልማት ባንክን የ2014 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።

በመድረኩ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ የተገኙ ሲሆን የባንኩ ላባለፈው በጀት ዓመት አፈጻጸምና ቀጣይ ስራዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በንግግራቸውም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከነበረበት ኪሳራ ለመውጣት በወሰዳቸው የለውጥ እርምጃዎች ስኬታማ መሆኑ የሚደነቅና አርዓያ የሚሆን ነው ብለዋል።

በተለይም በብድር አሰባሰብ የታየው አፈጻጸም ይበል የሚያሰኝ መሆኑን ጠቁመው ባንኩ ያገኘው ትርፍም የሚበረታታ እንደሆነ አንስተዋል።

አካታች የፋይናንስ ስርዓት መዘርጋትና ተሰብሳቢ ብድር ላይ ጠንካራ ስራ መስራት እንደሚኖርበትም ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈ የውጭ ምንዛሬ ግኝትና አቅርቦት ላይ ባንኩ በተሻለ መልኩ መንቀሳቀስ እንደሚገባው አጽንኦት ሰጥተዋል።

የመንግስት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር የፋይናንስ ድርጅቶች ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰውአገኝ ጫኔ፤ በባንኩ አፈጻጸም ዙሪያ የተዘጋጀውን ግብረ መልስ አቅርበዋል።

ባንኩ ባዘጋጀው ቦንድ ሽያጭ አሰራር በ2014 ዓ.ም 10 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡ የላቀ አፈፃፀም መሆኑን ነው ያነሱት።

ባንኩ ብድር አሰባሰብ ላይ 12 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ እቅድ ይዞ 10 ነጥብ 9 ቢሊየን መሰብሰቡን የገለጹት አቶ ሰውአገኝ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ባንኩ ብድር ክትትል ላይ አሁንም የበለጠ መስራት እንደሚገባው የጠቁሙት ዋና ሥራ አስፈጻሚው በሊዝ ፋይናንስ ላይ የታየው አፈጻጸም ሊሻሻል ይገባል ብለዋል።

የኢንተርኔትና የሞባይል ባንኪንግ አሰራር ፈላጊዎች ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ ባንኩ እነዚህንም አሰራሮች ማካተተት ላይ ትኩረት መስጠት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሃንስ አያሌው፤ ባንኩ ባለፈው ዓመት 3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ከታክስ በፊት ማትረፍ መቻሉን አታውቀዋል።

ባንኩን ለኪሳራ የዳረጉ ምክንያቶች ምን ምን ናቸው የሚለውን በጥልቀት ማየት መቻሉ ለተገኘው ውጤት ምክንያት መሆኑንም አብራርተዋል።

የባንኩ አሰራር፣ የቢዝነስ ሞዴሎችና መሰል አሰራሮች ላይ የለውጥ ስራዎች መካሄዳቸውንም ነው ፕሬዝዳንቱ የጠቀሱት።

ልማት ባንክ 6 ቢሊዮን የሚያወጡ ፕሮጀክቶችን እንደ ገና ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉንም ከቁልፍ ስኬቶቹ መካከል መሆኑን ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም