ቀጥታ፡

በጋሞ ዞን በተጠናቀቀዉ የበጀት ዓመት ከቱርዝም ከ160 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል--መምሪያው

አርባ ምንጭ ነሐሴ 19/2014 (ኢዜአ) በተጠናቀቀው የ2014 በጀት ዓመት ከቱሪዝም ዘርፍ ከ160 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የጋሞ ዞን ባህልና ቱርዝም መምሪያ አስታወቀ፡፡

በበጀት ዓመቱ አከባቢውን ከጎበኙ ከ263 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች ገቢው መገኘቱን መምሪያው አስታውቋል፡፡

የመምሪያው ሃላፊ አቶ ሙናዬ ሞሶሌ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ቱሪዝም የአገር ኢኮኖሚንና ገጽታን በመገንባቱ ጉልህ ድርሻ ያለው በመሆኑ መንግስት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡

"ጋሞ ዞን የዓለም አቀፍ መስህብነት ደረጃን ያሟሉና ለጎብኚዎች ሳቢ የሆነ ተፈጥሮአዊና ባህላዊ ይዘት ያላቸው በርካታ የቱሪስት መዳረሻ ይገኛሉ" ብለዋል፡፡

የስምጥ ሸለቆ ትሩፋት የሆኑ አባያና ጫሞ ሃይቆቸ፣ የአርባ ምንጭ አዞ ራንች፣ ነጭ ሳርና ማዜ ብሔራዊ ፓርኮች ከመስቦች መካከል መሆናቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል ፡፡

"በእርጥብ ሳር ጸብን የማብረድና 'ዱቡሻ' የተሰኘው ባህላዊ የእርቅ ስነ-ስርአት፣ የሽመና ጥበብ፣ ገዳማት፣ ፍል ውሃዎችና ሌሎች መስህቦች እንደሚገኙ አቶ ሙናዬ ሞሶሌ ጠቅሰዋል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ263 ሺህ በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች አከባቢውን መጎብኘታቸውን ጠቅሰው የጎብኚዎቹ ቁጥር ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር 20 በመቶ ወይም ከ46 ሺህ በላይ ብልጫ እንዳለው አስታውቀዋል፡፡

ከጎብኚዎቹ ከ160 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ጠቅሰው ባለፈው አመት ከዘርፉ ከተገኘው የ50 በመቶ ወይም ከ53 ሚሊየን ብር በላይ ብልጫ ማሳየቱን አስረድተዋል፡፡

በሀገሪቱ ሰላም እየተረጋገጠ መምጣቱና የኮሮና ወረርሽኝ ተጽኢኖ መቀነስ በዘርፉ ለተመዘገበው እድገት  ሚናቸው ከፍተና ነው ብለዋል፡፡

በዞኑ በርካታ የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መኖሩን የገለጹት አቶ ሙናዬ የጋሞ ዞን መስተዳድር የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት ለቱሪስት ምቹ እያደረገ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

በዞኑ የሚገኙ መስህቦችን ለመጎብኘት የመጡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ዶክተር አለማየሁ ንጋቱ ጭስ አልባ ኢንዱስትሪ የሆነው ቱሪዝም ዘርፍ የአገርን ኢኮኖሚ ከመገንባቱ በላይ አገርን በማስተዋወቅና ገጽታን በመገንባት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡

"በአገራችን የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች በአግባቡ ባለመልማታቸው ተገቢውን ጥቅም እያገኘን አይደለም" ያሉት ዶክተር አለማየሁ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን ምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳቸውን ማጎልበት ላይ ሊሰራ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

የአርባ ምንጭ አዞ ራንች፣ አባያና ጫሞ ሀይቆችና አርባዎቹን ምንጮች በመጎብኘታቸው እንደተደሰቱ የተናገሩት ደግሞ ተማሪ ቱብስት ታደሰ ናት፡፡

"በክረምት እረፍት ጊዜያቸው ከቤተሰቦቼ ጋር የጉብኝት ዕድል በማግኘቴ ስለ አገራችን የቱሪስት ሀብቶች ግንዛቤ እንዲኖረኝ አግዞኛል" ብላለች፡፡

ከውጭ የሚመጡ ቱሪስቶች ስለ አገራችን መስህብ ቦታዎች የተሻለ ዕውቀት እንዳላቸው መታዘቧን ገልጻ "አኛ የራሳችንን ታሪካዊ ቅርሶችንና መስህቦችን ማወቅና መንከባከብ ይጠበቅብናል" ስትል ነው የተናገረችው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም