ደብሊውኤፍፒ በአሸባሪው ህወሃት የተዘረፈበት ነዳጅ ካልተመለሰ የሰብአዊ ድጋፍ ለማከናወን እንደሚፈተን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ደብሊውኤፍፒ በአሸባሪው ህወሃት የተዘረፈበት ነዳጅ ካልተመለሰ የሰብአዊ ድጋፍ ለማከናወን እንደሚፈተን አስታወቀ
ነሐሴ 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአለም ምግብ ፕሮግራም (ደብሊውኤፍፒ) በአሸባሪው ህወሃት የተዘረፈበት 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ ካልተመለሰ የሰብአዊ ድጋፍ ለማከናወን እንደሚፈተን አስታወቀ።
የደብሊውኤፍፒ ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ባስሊ ለሰብአዊ ድጋፍ አገልግሎት ለማዋል በመቀሌ የተቋሙ መጋዘን ውስጥ ተከማችቶ የነበረውንና በህወሃት ታጣቂዎች የተዘረፈውን ነዳጅ አስመልክቶ መግለጫ አውጥተዋል።
በመግለጫቸውም የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብአዊ ድጋፍ ሲል አሳልፎት የነበረው የተኩስ ማቆም ውሳኔ ባለፉት ወራት በትግራይ ክልል አምስት ሚሊዮን ለሚሆኑ የሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ፈጥሮለት ነበር።
በደብሊውኤፍፒ የመቀሌ መጋዘን በቅርቡ የደረሱ ከግማሽ ሚሊዮን ሊትር በላይ የያዙ 12 ሙሉ ታንከሮችን ረቡዕ ማለዳ የታጠቁ ሃይሎች በሃይል ገብተው መዝረፋቸውን ገልጸዋል።
ደብሊውኤፍፒ ከዚህ ነዳጅ ውጪ ምግብ፣ የአፈር ማዳበሪያ፣ መድሃኒትና ሌሎች የአስቸኳይ ድጋፍ ቁሳቁሶችን በትግራይ ክልል ለማሰራጨት እንደሚፈተን ጠቁመው፤ ደብሊውኤፍፒ ተሽከርካሪዎችና ጀኔሬተሮችን ለማንቀሳቀስእንደሚቸገር ገልጸዋል።
በመሆኑም ደብሊውኤፍፒ እና ሌሎች አጋሮች በትግራይ ክልል የሚደግፏቸው 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች ለከፋ አደጋ እንደሚጋለጡ አመልክተዋል።
በመሆኑም ዘረፋውን የፈጸመው ቡድን ነዳጁን እንዲመልስ አሳስበዋል።