ቀጥታ፡

ኮንትሮባንድን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተጀመረው ቅንጅታዊ ስራ ውጤት እያሳየ ነው-ኮሚሽኑ

ሐዋሳ ነሐሴ 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በሀገር ኢኮኖሚ እና በህዝብ ደህንነት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት በዘላቂነት ለመከላከል የተጀመረው የቅንጅት ስራ አበረታች ውጤት እያስገኘ መሆኑን የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን፣ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን እና ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር የ2014 በጀት ዓመት ዓመታዊ የኮንትሮባንድ መከላከል የእቅድ አፈፃጸም ግምገማ  በሀዋሳ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የኢንተለጀንስ ዳይሬክተር አቶ ተገኔ ደረሰ ለኢዜአ እንዳሉት የኮንትሮባንድ ፍሰት በሀገር ኢኮኖሚ እና በህዝብ ደህንነት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ኮሚሽኑ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ ነው።

ክልሎችን ያካተተ የፀረ ኮንትሮባንድ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ወንጀሉን ለመከላከልና ለመቆጣጠር  ያላሰለሰ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

እየተደረገ ባለው ጥረት አበረታች  ውጤት መገኘቱን  ጠቅሰው  በተለይ  በ2014 በጀት  ዓመት ኮንትሮባንድና ንግድ ማጭበርበርን ለመከላከል በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን አመልክተዋል፡፡

በ2014 በጀት ዓመት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በህግ በማስከበር፣ በድንገተኛ ፍተሻ፣ በንግድ ማጭበርበርና በቀረጥ ነፃ መብት ሽፋን የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን  በጥንካሬነት አንስተዋል።

በተለይ የፍትህ ሚኒስቴር የአቃቤ ህግ ባለሙያዎችን  በየክልሉ ባሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በቅርበት እንዲሰሩ በመመደቡ ተጠርጣሪዎችን በህግ ፊት አቅርቦ አስተማሪ ቅጣት እንዲቀጡ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቁመዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለሀገርና ህዝብ ደህንነት ስጋትና ጠንቅ የሆኑ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ፣ወጣቱን ለወንጀል የሚያነሳሱና ከስራ ውጭ የሚያደርጉ አደንዛዥ ዕጾች፣ የተበላሹና ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶችን በመያዝ የዜጎችን ህይወት መታደግ መቻሉን በጠንካራ ጎን መገምገሙን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ የገቢና ወጪ ኮንትሮባንድን ለመከላከል በተደረገው ጥረት 5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የእቃዎች መያዛቸውን ጠቁመው አፈጻጸሙም ከእቅዱ 12 በመቶ ብልጫ እንዳለው  አስታውቀዋል።

ባንጻሩ የስነ ምግባር  እና የሌብነት  ችግር መኖር  በዘርፉ በድክመት  የታዩ  ክፍተቶች  መሆናቸውን ጠቁመው  በዚህ ረገድ መረጃ አሳልፎ መስጠት፣ጉቦ መቀበል፣ በኔትወርክ ተደራጅቶ መስረቅና ለኮንትሮባንዲስቶች ሽፋን መስጠትን ለአብነት አንስተዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች የነበሩ  የፀጥታ ችግሮችም በተግዳሮትነት መታየታቸውን ጠቅሰዋል ።

በቀጣይ የኮንትሮባንድ መከላከልና መቆጣጠር ሂደቱን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት በየደረጃው ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ   መመላከቱን ገልጸዋል ።

እንዲሁም ኮንትሮባንድ መከላከል ስራውን የሚያግዙ አስፈላጊ ግብዓቶች ማሟላት፣  አስፈላጊ የሆኑና ያልሆኑ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎችን በመለየት ማስተካከያ ማድረግ  በመፍትሄነት መካተታቸውን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።   

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ ኮንትሮባንድና ድንበር ቁጥጥር ፖሊስ  ምክትል መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር መስፍን አመንሲሳ በሰጡት አስተያየት የኮንትሮባንድ ፍሰት በሀገር ኢኮኖሚና በህዝብ ጤና ላይ ዘርፈ ብዙ ጉዳት እንዳያስከትል ፖሊስ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በጉምሩክ ኬላዎች ላይ የሰው ሃይል ከመመደብ ባሻገር በበረራና በደፈጣ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ቅኝት በማድረግና ኮንትሮባንዲስቶችን አሳዶ በመያዝ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመግታት ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተደረገው እንቅስቃሴ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ የተከለከሉ፣ ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልባቸው  ከሀገር እንዳይወጡ የተከለከሉ በርካታ እቃዎች መያዝ መቻሉን  አስታውቀዋል።

ከተያዙት መካከል ለጤና ጠንቅ የሆኑ ምግብ ነክ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ እቃዎች፣ ሺሻ፣ አደንዛዥ እጽ፣ ሲጋራ፣ ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶችን ጠቅሰዋል።

በጥቅም በመደለል ኮንትሮባንድን የመከላከሉን ስራ ባስተጓጎሉና የስነ ምግባር ችግር ያለባቸውን አባላት ከስራ በማገድ  በህግ እንዲጠየቁ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም