ቀጥታ፡

ካሜሮን ከኢትዮጵያ ጋር በአምራች ኢንተርፕራይዙ ዘርፍ በትብብር መስራት እንደምትፈልግ ተገለጸ

ነሐሴ 19/2014(ኢዜአ) ካሜሮን ከኢትዮጵያ ጋር በአምራች ኢንተርፕራይዙ ዘርፍ በተጠናከረ ትብብር መስራት እንደምትፈልግ ተገለጸ።

የኢትዮጵያን የአምራች ኢንተርፕራይዞች ልማት ተሞክሮ ለመቅሠምና በዘርፉ ተባብሮ ለመስራት ያለመ የካሜሮን የልዑክ ቡድን ከኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር ብሩ ወልዴና ከተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያይቷል፡፡

የልኡክ ቡድኑ መሪ አቦ ሶሎ በወቅቱ እንደገለፁት ካሜሮን ኢትዮጵያ በአምራች ኢንተርፕራይዞች ዘርፍ እያመጣችው ካለው ስኬት በብዙ መማር ትፈልጋለች፡፡

ይህንን ስኬትም በተጠናከረ ኢኮኖሚያዊ ትብብርና ተሞክሮ ልውውጥ በማጀብ አፍሪካዊ ወንድማማችነትን ለማፅናት ፍላጎቱ አላት ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ብሩ ወልዴ በበኩላቸው እንዳሉት ኢትዮጵያ ሰፊ ተፈጥሯዊ ሀብቷን፣ የተማረ ወጣትና አነስተኛ የፋይናንስ አቅም ታሳቢ ያደረገ የአምራች ኢንተርፕራይዞች ልማት ተግብራለች።

በዚህም በአስርሺዎች የሚቆጠሩ አምራች ኢንተርፕራይዞችንና በርካታ የስራ ዕድልን ለመፍጠር ችላለች ነው ያሉት፡፡

እነዚህን ስኬቶች ለማስፋትም ተቋሙ በተለይ በመስሪያ ቦታ፣ በግብዓትና በፋይናንስ አቅርቦት በኩል ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ዘላቂነት ያላቸውን ስልቶች ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት በታሕሳስ አጋማሽ በካሜሩን በሚካሄደው የካሜሩን – ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትስስር ባዛር ላይ ተቋሙ እንዲሳተፍና ተሞክሮውን እንዲያካፍል የልኡክ ቡድኑ ጋብዟል፡፡

የልዑክ ቡድኑ በተጨማሪም በተቋሙ የሚገኘውን የፈጠራ ማዕከል ጎብኝቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም