የዞኖቹ የጋራ ጥምር ኮሚቴ ከደብረ ብርሃን እስከ አዲስ አበባ የፍተሻ ኬላዎችን በማጠናከር ውጤታማ የፀጥታ ጥበቃ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የዞኖቹ የጋራ ጥምር ኮሚቴ ከደብረ ብርሃን እስከ አዲስ አበባ የፍተሻ ኬላዎችን በማጠናከር ውጤታማ የፀጥታ ጥበቃ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ
ነሀሴ19/2014ኢዜአ/በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ፣ የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን እና በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞኖች የጋራ ጥምር ኮሚቴ ከደብረ ብርሃን እስከ አዲስ አበባ የፍተሻ ኬላዎችን በማጠናከር ውጤታማ የፀጥታ ጥበቃ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።
ከደብረ ብርሃን እስከ አዲስ አበባ ባለው መንገድ የጥፋት ተልዕኮ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ለመቆጣጠር በተደረገ ፍተሻ የተፈጠረው የመንገደኞች መስተጓጎልና መጉላላት ችግር መቀረፉንም የዞኖች ጸጥታ ጥምር ኮሚቴ ገልጿል።
መንግስት የሕወሃት፣ የሸኔ፣ አልሸባብና መሰል አሸባሪ ኃይሎች በአዲስ አበባ እና በፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ባሉ ከተሞች ላይ መሽገው አገር የማተራመስ ፍላጎት እንዳላቸው መግለጹ ይታወሳል።
ሀሰተኛ ገንዘብ ዝውውር፣ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ እና የሰዎች ዝውውር እንዲሁም ሌሎች ልዩ ልዩ ወንጀሎችን የሚፈጽሙ ሰርጎ ገቦችን ለመቆጣጠርም ጥብቅ የጸጥታ ስራዎችን እየተከናወኑ ነው ተብሏል።
በፌዴራልና የክልል መንግስታት በተላለፈው ውሳኔ መሰረት ጥብቅ የጸጥታ ቁጥጥር ከሚደረግባቸው መንገዶች አንዱ ከሰሜን ወሎ እስከ አዲስ አበባ ያለው ጎዳና ነው።
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ፣ የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን እና በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አመራሮች የጋራ ጥምር ኮሚቴ መስርተው እየሰሩ ሲሆን፤ የሶስቱ ዞኖች አመራሮች ከደብረ ብርሃን እስከ አዲስ አበባ ያሉ የፍተሻ ኬላዎችን ተመልክተው፤ የቀጣይ ቅንጅታዊ ዕቅዶች ላይ ተወያይተዋል።
ኢዜአም በስፍራው ተገኝቶ የሶስቱ ዞኖች ጥምር ኮሚቴ ሰብሳቢና የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግርማ ኃይሉ፣ በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ክፈለው አደሬና የደብረ ብርሃን ከተማ ከንቲባ አቶ ካሳሁን እምቢያለን በጉዳዩ ላይ አነጋገሯል።
አመራሮቹ እንዳሉት አጎራባች የመንግስት መዋቅሮች ዕኩይ ዓላማ ያላቸውን ኃይሎች እንቅስቃሴ ለመግታትና በቀጣናው የሚስተዋሉ ልዩ ልዩ ወንጀሎችን ለመከላከል በጋራ ሲሰሩ ቆይተዋል።
ከደብረ ብርሀን እስከ አዲስ አበባ በተከናወኑ ጠንካራ የሰላምና ጸጥታ ቁጥጥር ስራዎችም ወደ አዲስ አበባ ገብተው ጥፋት ሊፈፅሙ የነበሩ ተጠርጣሪዎችና ሕገ ወጥ ጦር መሳሪያዎች ተይዘዋል ነው ያሉት።
በቅርቡ ህዝብ የሚያጉላሉ ሁኔታዎች የተፈጠሩት ከፍተሻ ፖሊሶች ቁጥር ማነስና የመንገደኞች ብዛት ችግር እንጂ ማንነትን መሰረት ያደረገ መጉላላት እንዳልነበር ገልጸዋል።
ሕጻናትንና አዛውንቶችን ጨምሮ በርካታ ዜጎች በመጉላላታቸው ቅሬታ መፈጠሩን አውስተው፤ የአጎራባች ዞኖች አመራሮች የተፈጠረውን ችግር ገምግመው ችግሩ እልባት እንደተሰጠው ተናግረዋል።
በጥፋት ተልዕኮ የተጠረጠረ አካል በተያዘበት ቆይቶ መመርመር እንዳለበትና ሌሎች መንገደኞች ግን መጉላላት ሳይደርስባቸው እንዲንቀሳቀሱ የጋራ ግምገማ ተወስዶ ችግሩ መቀረፉንም ገልጸዋል።
ማንኛውም ሰላማዊ ዜጋ በየትኛው የአገሪቷ አካባቢ የመዘዋወር መብቱ እንደማይገደብ ገልጸው፤ህዝብ የሚያስኮርፉ ሁኔታዎች መስተካከላቸውንም እንዲሁ።
በሌላ በኩል ገንዘብ እየተቀበሉ ያሳልፋሉ በሚል በማህበራዊ ሚዲያ የሚናፈሰው መረጃ እስካሁን በተደረገ ማጣራት ተጨባጭ ማስረጃ አለመኖሩን ገልጸው፤ መንገዱ ተዘግቷል የሚለውም ከዕውነት የራቀ መረጃ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በአጠቃላይ የፍተሻና ጥበቃ ስርዓቱን በማሻሻል መንገደኞች ሳይጉላሉ ውጤታማ የሰላምና ጸጥታ ስራዎችን ለመስራት በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን የዞኖቹ አመራሮች ገልጸዋል።
ተጨማሪ የጸጥታ ኃይል የማሰማራት፣ የስነ ምግባር ጉድለት ያለባቸውን የጸጥታ አካላትም እርምጃዎች እንደተወሰደም ነው የተናገሩት።
ህብረተሰቡም የተጠናከረው የፍተሻ ስራ ለሀገር ሰላምና ደህንነት ሲባል መሆኑን አምኖ ለጸጥታ ኃይሉ ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራና ኦሮሞ ህዝብ ሁለንተናዊ ትስስር ያላቸውና ተጋምደው የኖሩ፣ እጣፈንታቸውም አብሮነት እንደሆነ ገልጸው፤ ይህን የሚጻረር አመራርና የጸጥታ አባል ላይ ጥብቅ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
ጥምር ኮሚቴው በቀጣይ ዕቅዱም በተጠኑ ቦታዎች ፍተሻዎችን ማካሄድ፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መድረኮችን ማዘጋጀት፣ የፀጥታ አካላት ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር፣ ስነ ምግባር የተላበሱ ፖሊስ አባላትን መመደብ፣ የተሽከርካሪ ታርጋ ተኮርና መሰል የሚያጋጥሙ ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደ መፍትሔ ተወስደዋል።