ቀጥታ፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ገለጸ

ነሐሴ 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በተጠናቀቀው 2014 በጀት ዓመት 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ገልጿል።

በዚህም ከ340 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገቡም ነው የጠቀሰው።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ፤ የ2014 በጀት ዓመት አፈጻጸምን አስመልክቶ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የተሰማሩ ባለሃብቶች ወደ ውጭ ከላኳቸው ምርቶች 196 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል።

አፈጻጸሙም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የስምንት በመቶ ብልጫ እንዳለውም አንስተዋል።

ለሀገር ውስጥ ገበያ ስትራቴጂካዊ ምርቶችን በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ጫናን ለመቀነስ መሰራቱን ተናግረዋል።

May be an image of 8 people, people sitting, people standing, suit and indoor

በዚህም 161 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መተካት መቻሉን ጠቅሰዋል።

ከሀገር ውስጥ ምርት አቅራቢ ድርጅቶችና አርሶ አደሮች ጋር በተፈጠረ ትስስርም ከ69 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ ግብዓት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ለተሰማሩ የውጭ ኩባንያዎች ማቅረብ መቻሉን ተናግረዋል።

ኮርፖሬሽኑ በበጀት ዓመቱ ከመስሪያና መሸጫ ቦታ ኪራይ፣ ከቢሮ አቅርቦት እና ሌሎች አገልግሎቶች 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት አቅዶ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ጠቅሰው፤ በዚህም ከ340 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገቡን ገልጸዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ከአጎአ ተጠቃሚነት መሰረዟ፣ በሀገር ውስጥ በነበረው ጦርነት አምስት ኢንዱስትሪ ፓርኮች በስጋትና በደረሰባቸው ውድመት ማምረት ማቆማቸው ለኮርፖሬሽኑ ፈታኝ ሁኔታዎች ነበሩ ብለዋል።

የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦት አለመሟላት እንዲሁም የሩሲያና ዩክሬን ጦርነትም በበጀት ዓመቱ ያጋጠሙ ፈተናዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

የሀገር ውስጥ አልሚ ባለሃብቶች በወጭ ንግድና በተኪ ምርት ዘርፍ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ እንዲገቡ የማበረታታት ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ከ57 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም