ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን እምቅ የታዳሽ ኃይል ሀብት በማልማት ለሀገራዊ እድገትና ለቀጣናዊ ትስስር ማዋል ይገባል-ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ

ነሃሴ 19/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያን እምቅ የታዳሽ ኃይል ሀብት በማልማት ለሀገራዊ እድገትና ለቀጣናዊ ትስስር ማዋል እንደሚገባ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ ገለጹ።

ኢንጂነር ክፍሌ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ የሚኖረውን አገራዊና ቀጣናዊ ፋይዳ አብራርተዋል።

ግድቡ ከሀይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል በዓመት እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ዓመታዊ ገቢ እንደሚያስገኝ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከውሃ ብቻ እስከ 45 ሺህ ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ማመንጨት የምትችል መሆኑን ጠቁመው የጂኦ ተርማል፣ የፀሐይ እንዲሁም የነፋስ ኃይል ማመንጨት የሚያስችል እምቅ ሃብት አላት ብለዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በሌሎችም የልማት መስኮች ለቀጣናዊ የልማት ትስስር ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያ በሀይድሮ ኤሌክትሪክ ሀይል ከፍተኛ እምቅ ሀብት በመያዝ ከአፍሪካ ሁለተኛዋ ሀገር ብትሆንም፤ ከውሃ ሀብቷ የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ  መቆየቷን አንስተዋል።

በሂደትም በፍትሐዊ የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ በመመስረት በድንበር ተሻጋሪው የዓባይ ወንዝ ላይ የህዳሴ ግድቡን ግንባታ በማካሄድ ከውሃ ሀብቷ የኃይል ተጠቃሚ ለመሆን እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

ግድቡ በሁለት ዓመት ተኩል እንዲጠናቀቅ እየሰራን ነው ያሉት ኢንጂነር ክፍሌ፤ በአሁኑ ወቅት ሁለት ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።

በቀጣይ ግንባታው ሙሉ ቡሉ ሲጠናቀቅ እና 11 ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት ሲጀምሩ ኢትዮጵያ በዓመት እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢ እንደምታገኝ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ያሏትን የውሃ ሀብትና ሌሎች የታዳሽ ኃይል እምቅ ሀብት በማልማት ለሀገራዊ እድገትና ለቀጣናው የኢኮኖሚ ትስስር መጠናከር እንደምትሰራም ነው ያብራሩት።

ለዚህ ሀገራዊና ቀጣናዊ ሚና መሳካትና በህዳሴ ግድብ የተመዘገበው ድል በሌሎችም እንዲቀጥል በትብብር መስራት አለብን ብለዋል።

የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት የታችኞቹን የተፋሰስ ሀገራት በማይጎዳ መርህን ባከበረ መልኩ እየተከናወነ እንደሆነም አንስተዋል።

በዚህም ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ልማት ላይ የማዋል ሂደቱ የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረገ መልኩ እንዲከናወን ለሌሎች አርዓያ የሚሆን ተግባር መፈፀሟን በማንሳት።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ እና ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ይፋ መደረጉ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም