የህብረተሰቡን ጤና የሚጎዱ ምግብና መድሃኒትን በማምረትና በማከፋፈል ላይ የነበሩ ከ500 በላይ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ - ኢዜአ አማርኛ
የህብረተሰቡን ጤና የሚጎዱ ምግብና መድሃኒትን በማምረትና በማከፋፈል ላይ የነበሩ ከ500 በላይ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ
ነሀሴ 19/2014 /ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን የህብረተሰቡን ጤና የሚጎዱ ምግብና መድሃኒትን በማምረትና በማከፋፈል ላይ የነበሩ ከ500 በላይ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን ገለጸ።
እርምጃ ከተወሰደባቸው ድርጅቶች 388 በምግብ ዘርፍ የተሰማሩ ሲሆኑ ከ120 የማያንሱት ደግሞ በመድሃኒት ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች መሆናቸው ታውቋል።
ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅለው ለህብረተሰቡ ሲያሰራጩ የነበሩ አራት ግለሰቦችም የእስራትና የገንዘብ ቅጣት ተወስኖባቸዋል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሔራን ገርባ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ በ2014 በጀት ዓመት ለ4 ሺህ 510 አዲስ የምግብ ዓይነቶችን በመመዝገብ የገበያ ፈቃድ ተሰጥቷል።
ከዚህም ባሻገር ከ3 ነጥብ 6 ሚሊየን ቶን በላይ ምግብ ተገቢው ፍተሻ ተደርጎ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ ፈቃድ መስጠቱን ገልጸዋል።
ሆኖም በ118 የምግብ ዓይነቶች ላይ በላብራቶሪ የጥራት ምርመራ ተደርጎ 67ቱ መስፈርቱን ባለማሟላታቸው ለገበያ እንዳይቀርቡ መደረጉን ነው ያብራሩት።
ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅሎ ለገበያ በማቅረብ በተጠረጠሩ ተቋማትና የምግብ ዓይነቶች ላይ በተደረገ ቁጥጥር ከ247 የዱቄት፣ የካሳቫ ዱቄት፣ ማር፣ በርበሬ፣ ቅቤ ምርቶች ውስጥ 158 የሚሆኑት ባዕድ ነገር ተቀላቅሎባቸው በመገኘታቸው እንዲወገዱ መደረጉን ጠቅሰዋል።
የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን 388 የምግብ አምራች ድርጅቶች እና ጅምላ አከፋፋዮች ላይ የማስጠንቀቂያ፣ የንግድ ፈቃድ ስረዛና የእገዳ ርምጃ መወሰዱንም ገልጸዋል።
በባለስልጣኑ በተደረገው ቁጥጥር በሰው ልጅ ላይ ከፍተኛ የጤና ጉዳት ሊያደርስ የነበረ 670 ሺህ ቶን ምግብ እንዲወገድ መደረጉን ጠቅሰዋል።
በሐዋሳ ከተማና በሀላባ ቀለምና የበርበሬ ልቃሚን ቀላቅለው ለህበረተሰቡ ለማቅረብ ሲያዘጋጁ በነበሩ ሰዎች ላይ እርምጃ መወሰዱንም ጠቅሰዋል።
በዚሁ ተግባር ላይ ተሳትፎ የነበራቸው አራት ግለሰቦች ላይ ክስ በመመስረት ከሁለት ዓመት ከሶስት ወር እስከ አምስት ዓመት ተኩል እስራትና የገንዘብ ቅጣት የተወሰነባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በመድሃኒት ላይ በተደረገው ቁጥጥርም አጠቃላይ ግምታዊ ዋጋቸው 12 ሚሊየን 732 ሺህ በላይ የሚሆኑ የጥራት ደረጃን ያላሟሉ መድሃኒቶች ወደ ገበያ እንዳይቀርቡ መወገዳቸውን ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።
መድሃኒቶቹ የተገኙባቸው 120 ተቋማት ላይም እንደ ጥፋት ደረጃቸው የማስጠንቀቂያ፣ የእገዳና የንግድ ፈቃድ ስረዛ እርምጃ መወሰዱን ነው የተናገሩት።
በህክምና መሳሪያዎችና በውበት መጠበቂያ ቁሶች ላይ በደረገው ቁጥጥርም በርካታ የጥራት ጉድለቶች በመገኘታቸው ባለስልጣኑ እርምጃ ወስዷል ብለዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባለስልጣኑ ለመከላከያ ሰራዊትና ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች 12 ሚሊዮን ብር የሚገመት የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጉን አስታውቀዋል።