ቀጥታ፡

አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በተመረጡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሙከራ ትግበራ ይጀመራል-ትምህርት ሚኒስቴር

ነሐሴ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ)አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በሃገር አቀፍ ደረጃ በተመረጡ 80 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የማስተማር የሙከራ ትግበራ ለመጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ በሙከራ ትግበራ አጀማመር፣በተዘጋጁት የማስተማሪያ መጽሀፍትና በትምህርት አሰጣጥ ዙሪያ የአሰልጣኞች ሥልጠና በደብረ ብርሀን ከተማ እያካሄደ ነው።

በትምህርት ሚኒስቴር የሥርዓተ ትምህርት ማበልፀጊያ መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ቴዎድሮስ ሸዋርገጥ በወቅቱ እንዳሉት፤የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሥርዓተ ትምህርት ሪፎርም እየተካሄደ ነው።

በዚህም ከ2012 ዓም ጀምሮ የሥርዓተ ትምህርት ሰነዶች የሚያካትታቸው የተማሪ ባህሪያት፣የይዘት ፍሰት መርሀ ትምህርትና ሌሎች ዝግጅቶች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በ2014 የትምህርት ዘመን በመላ ሀገሪቱ በተመረጡ 589 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአዲሱ የሥርዓተ ትምህርት የመማር ማስተማር የሙከራ ትግበራ መከናወኑን አስረድተዋል።

ከመስከረም ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ ከሙከራ በመውጣት በመላ ሀገሪቱ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ይተገበራል ብለዋል።

በሁለተኛ ደረጃ ዘጠነኛና አስረኛ ክፍሎች ደግሞ በተመረጡ 80 ትምህርት ቤቶች የሙከራ ትግበራ ለመጀመር የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

ለዚህም የመማሪያና ማስተማሪያ መፅሃፍት ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰው፤ በ2016 ዓ.ም ደግሞ 11ኛና 12 ክፍል በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መስጠት እንደሚጀመርም ጠቁመዋል።

በዚህም ከክልሎች ለተውጣጡ የትምህርት ባለሙያዎች ጋር በሙከራ ትግበራ ለሚጀምሩ የአሰልጣኞች ስልጠና እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት የነበረው የትምህርትና ሥልጠና አሰጣጥ አጠቃላይ እውቀት ላይ ያተኮረ በመሆኑ የጥራት አግባብነት ችግር እንዳለበት ጠቅሰዋል።

አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ግን ተማሪዎች በሀገር በቀል እውቀት እንዲኖራቸው የግብረ ገብና የሥነ- ምግባር ትምህርትን ጨምሮ የሥራና ተግባር ትምህርት ያካተተ መሆኑን አብራርተዋል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክተር አቶ ካሳዬ አባተ በበኩላቸው፤በክልሉ በሚገኙ ሁሉም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ለማስተማር ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

በክልል ደረጃም የማስተማሪያ መጽሀፍት መዘጋጀቱን ጠቁመው፤ ከመጪው መስከረም ወር ጀምሮ ለሚካሄደው የዘጠነኛና አስረኛ ክፍል የሙከራ ትግበራ 17 ትምህርት ቤቶች ተለይተዋል ብለዋል።

በደብረ ብርሀን ከተማ ለሁለት ቀናት በሚቆየው ሥልጠና ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ከ300 በላይ የትምህርት ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም