ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በጫናዎችም ውስጥ ሆና በህዳሴ ግድብ ግንባታ ትልቅ ድልና ስኬት አስመዝግባለች- የህግ ምሁራን

ነሐሴ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በብዙ ጫናዎችም ውስጥ ሆና በህዳሴ ግድብ ግንባታ ትልቅ ድልና ስኬት ማስመዝገቧን ኢዜአ ያነጋገራቸው የህግ ምሁራን ገለጹ፡፡

በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከጅምሩ የተሳሳተ አቋም የምታራምደው ግብፅ ግንባታውን ለማስተጓጎል በማሰብ ያላደረገችው ጥረት የለም።

በዚሁ ዙሪያ በኢትዮጵያ ላይ የዲፕሎማሲና ሌሎች ተጽእኖዎችን ለማሳረፍ እስካሁንም የዘለቀ ተደጋጋሚ ሙከራ እያደረገች ትገኛለች።

ለዚህም ይረዳት ዘንድ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ አገራትና ተቋማት፣ በውሃ አጠቃቀሙ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ሕጋዊ እና አሳሪ ስምምነት እንዲደረስ "አግዙኝ በሚል ድብቅ ሴራ" የበርካቶችን በር ማንኳኳቷን ቀጥላለች።

በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ግብፅ ስምምነት ሳይደረስ ኢትዮጵያ ግድቡን ውሃ መሙላት አትችልም በሚል ተቃውሞና ማስጠንቀቂያ ስትሰነዝር ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡

ነገር ግን የውሃ ሙሌቱ የግንባታው ተፈጥሯዊ ሂደት መሆኑንና ጥያቄውም ተቀባይነት እንደሌለው በመግለጽ ኢትዮጵያ ሶስት ዙር የውሃ ሙሌት በተሳካ መንገድ ማካሄዷን አሳውቃለች።

ኢትዮጵያ ግድቡ ለኤሌክትሪክ ማመንጫነት የሚውል በመሆኑ በታችኛው የተፋሰሱ አገራት ላይ የጎላ ጉዳት ስለማያመጣ በውሃው የመጠቀም መብቷን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ግዴታን እንደማትፈርም አስረግጣ አስረድታለች።

በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የህግ ምሁራን ኢትዮጵያ በፈተና ውስጥ ብትሆንም በጽኑ አቋምና ጥንካሬ ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስከበር የሄደችበት ርቀት የሀገር የልማት መሰረት መሆኑንና ህዝብንም ያኮራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የህዳሴ ግድብ ግንባታ የደረሰበት ደረጃም ለኢትዮጵያ የተሻለ የመደራደር አቅምን የሚፈጥርና የስኬት እርካብ ላይ እየወጣች መሆኑን የጅንካ ዩኒቨርሲቲ  የህግ ትምህርት ክፍል ሀላፊ  ተሻለ ሻምበል ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ የመጠቀም ህጋዊ መብት ቢኖራትም የጎረቤት ሀገራትን ተጠቃሚነት ከግምት በማስገባት ለጋራ እድገት የጋራ መፍትሄ እንዲመጣ ያደረገችው ጥረት ቦታ በማጣቱ የራሷን አካሄድ መከተሏ አለም አቀፍ ህጎች የሚደግፉት መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል ዲን ታመነ ኤና በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ከ65 በመቶ በላይ በጨለማ ውስጥ የሚኖረውን ሕዝቧን ብርሃን ለማሳየትና ኢንዱስትሪዋን ለማጠናከር የምትጠቀምበት ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ግድቡ ግንባታ አሁን ለደረሰበት ስኬት ህዝቡ በሞራል፣ በእውቀት፣ በገንዘብና በጉልበት ያደረገው ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን በማንሳት ድጋፉ በቀጣይም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የህዳሴ ግድቡ ህዝቡን ከላይ እስከ ታች አንድ ማድረጉን በማውሳት የተደቀኑብንን ፈተናዎች በማለፍ ለዛሬ ስኬት የመብቃታችን ምስጢሩ አንድነታችን ነው ያሉት ደግሞ የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል ምክትል ዲን ደሊል ወርቂቾ  ናቸው፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድቡ ግንባታ 11 ዓመታት ጉዞ ህብረተሰቡ በቦንድ ግዥና በልገሳ 17 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን መረጃዎች ያሳያሉ።

አርሶ አደርና አርብቶ አደሩ በጉልበቱ የተፋሰስ ልማት ስራ በማከናወን በገንዘብ 121 ሚሊዮን ብር የሚገመት የጉልበት አስተዋጽኦ ማድረጉም ተገልጿል።

ኢትዮጵያ በፍትሀዊ የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመስርታ በአባይ ወንዝ ላይ እያከናወነችው ያለው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በመጪው 2 አመታት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም