ቀጥታ፡

በሚቀጥሉት 4 ዓመታት በፋይናንስ ዘርፍ 70 በመቶ ጎልማሶችን ለማካተት እየተሰራ ነው- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ

ነሐሴ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሚቀጥሉት 4 ዓመታት በፋይናንስ ዘርፍ 70 በመቶ ጎልማሶችን ለማካተት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገለጸ ።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ፋይናንስ አካታችነት ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ዘለቀ በ2014 በጀት ዓመት በዘርፉ በተከናወኑ ተግባራትና የተገኙ ውጤቶችን በሚመለከት መግለጫ ሰጥተዋል።        

በኢትዮጵያ በፋይናንስ ስርዓቱ ውስጥ የተካተቱ ወይም የባንክ ሂሳብ ያላቸው ዜጎች ከ45 በመቶ እንደማይበልጡ ገልጸው ይህም ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አሁን ላይ በሀገሪቱ 30 ሚሊዮን ገደማ የሚጠጋው ጎልማሳ በፋይናንስ ተቋማት ምንም ዓይነት ሂሳብ እንደሌለውም አስረድተዋል።     

የፋይናንስ ተቋማት ቅርንጫፎች ፣ወኪሎች ፣ኤቲ ኤምን ጨምሮ ፖስ ማሽኖች በገጠሩ የአገሪቷ ክፍል በሚፈለገው ደረጃ አለመሰራጨታቸውን በምክንያትነት አስቀምጠዋል።   

የጥቃቅንና አነስተኛ የቁጠባና የብድር ሰጪ ተቋማትን ጨምሮ የኢንሹራንስ አገልግሎት ሰጪዎች ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ማህበረሰብ ታሳቢ በማድረግ በኩል ውስንነት እንዳለባቸው አብራርተዋል።

በተለይም በገጠሩ አካባቢ ያለው የፋይናንስ እውቀትና ክህሎት ዝቅተኛነት ሌላው ምክንያት መሆኑን ዳይሬክተሩ አመላክተዋል።     

በመሆኑም መሰል ችግሮችን ለመፍታት ስትራቴጂ ጸድቆ ወደ ሥራ መገባቱን አብራርተዋል።           

ስትራቴጂው ከያዛቸው ቁልፍ ጉዳዮች መካከል የዲጂታል ወኪሎችንና የሴቶች ፋይናንስ አካታችነት እንዲሁም ከወለድ ነጻ አገልግሎቶች እንዲስፋፉ መስራት መሆኑን ተናግረዋል።

ቁጠባ፣ ብድር፣ መድንን ማስፋፋት የስትራቴጂው ምሰሶዎች እንደሆኑም ነው የገለጹት።   

በ2014 በጀት ዓመት የሞባይል ገንዘብ ዝውውር 170 በመቶ እድገት ማሳየቱን ገልጸዋል።

በሰኔ 2013 ዓ.ም 92 ሚሊዮን የነበረው የግብይት ሂሳብ ቁጥር እስከ ሰኔ 2014 ዓ.ም 131 ሚሊዮን ከፍ ብሏል ብለዋል።    

ከዚህ ባለፈም ፋይናንስ ተቋማት ቅርንጫፎች፣ ወኪሎች እንዲሁም ፖስና ኤት ኤም ማሽኖች ተደራሽነት ላይ እድገት መታየቱን አክለዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም