ቀጥታ፡

ኢህአዴግ በቡራዩና አከባቢው በህይወትና በንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገለጸ

መስከረም 8/2011 የኢትዮጵያ ህዝቦች  አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር/ ኢህአዴግ/ ሰሞኑን በቡራዩና አካባቢው በተፈጠረው ግጭት በህይወትና በንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገለጸ። የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽ/ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እዳመለከተው ባለፉት ቀናት በቡራዩና አካባቢው ባጋጠመው ሁከትና ግርግር በህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ ህገ ወጥ ድርጊቱ እየተፈፀመ ያለው ኢህአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ ካካሄደ በኃላ በድርጅቱ ሊቀመንበርና በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መሪነት በርካታ ለውጦች እየተመዘገቡና ህዝቡም ከመንግስት ጎን ተሰልፎ ለውጡን ለማስቀጠል እየተረባረበ ባለበት ወቅት መሆኑ በመግለጫው ተጠቅሷል ፡፡ በለውጡ ሂደት አመርቂ ስራዎች እየተከናወነ ቢሆንም  ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ በአንዳንድ የሀገሪቱ አከባቢዎች ስርዓት አልበኝነት በስፋት እየተስተዋለ መሆኑም በመግለጫው ተገልጿል። ስርዓት አልበኝነትን ለመግታትና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ኢህአዴግ የበኩሉን ሚና ለመወጣት ቁርጠኛ መሆኑን ድርጅቱ  በላከው መግለጫ ገልጿል።፡፡ ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር በህይወትና በንብረት ላይ ጥቃት ያደረሱ አካላት በህግ እንዲጠየቁ እንደሚሰራ  የገለፀው ድርጅቱ  የጥቃቱ ሰለባ ለሆኑ ቤተሰቦች  መጽናናትን ተመኝቷል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም