የኢትዮጵያ ፍራፍሬ እንዲሁም የሥጋ ምርት በቻይና ገበያ ለማስተዋወቅ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፍራፍሬ እንዲሁም የሥጋ ምርት በቻይና ገበያ ለማስተዋወቅ እየተሰራ ነው
ነሐሴ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፍራፍሬ እንዲሁም የሥጋ ምርት በቻይና ገበያ ለማስተዋወቅ እየተሰራ መሆኑን በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ገለጹ።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2018 ዓ.ም የተመሰረተው የቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም ተከትሎ ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት አስመልክቶ ተከታታይ ሪፖርት ለማውጣት ቃል በገባቸው መሰረት ሁለተኛውን ሪፖርት በትላንትናው ዕለት ይፋ አድርጋለች።
በቻይና ቤጂንግ በተካሄደው መርኃ ግብሩ ላይ የተሳተፉት አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር እየሰራች ነው።
ኢትዮጵያና ቻይና ጠንካራ የኢኮኖሚ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸው በተለይም በ“ቤልት ኤንድ ሮድ” በተሰኘው የቻይና ግዙፍ የመሰረተ-ልማት ፓኬጅ ሥር ኢትዮጵያም ተጠቃሚ መሆኗን ተናግረዋል።
ይህንንም ተከትሎ የአዲስ አበባ-ጅቡቲ የምድር ባቡርና ወደ ሥራ የገቡትን 7 የኢንደስትሪ ፓርኮችና በግንባታ ላይ የሚገኙትን ተጨማሪ 7 የኢንደስትሪ ፓርኮች ለአብነት አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በአገሪቱ እውን ለማድረግ ያሰበችውንና ቴክኖሎጂና ግዙፍ ኢንቨስትመንት የሚጠይቀውን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ለማረጋገጥ ከቻይና ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።
አሁን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የኢትዮጵያን የግብርና ምርቶች ለዓለም ለማስተዋወቅ ያሰቀመጡትን አቅጣጫ ተከትሎ የኢትዮጵያን የፍራፍሬና የሥጋ ምርት ለቻይና ገበያ ለማስተዋወቅ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።
ለአብነትም የኢትዮጵያን አቮካዶ፣ ሙዝና ማንጎ የመሰሉ ፍራፍሬዎች ወደ ቻይና ለማቅረብ ውይይት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በትላንትናው ዕለት ይፋ የሆነው ሪፖርት የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ኤምባሲዎች፣ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎችና በርካታ የሚመለከታቸው አካላት አስተያየትና ሃሳብ እንዲሁም አሃዛዊ መረጃዎች ተካተውበታል ተብሏል።
ሪፖርቱ የቻይናና የአፍሪካ የንግድ ትብብር እንዲሁም የቻይና ኩባንያዎች የአፍሪካን የአቅርቦት ሠንሰለት ልማት በመደገፍ ረገድ ያላቸውን ሚና እንዲሁም በሂደቱ ያጋጠማቸውን ችግሮች ዳሷል።
የቻይና ግዛቶች ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላቸውን ግንኙነትና ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ከአቅርቦት ሠንሰለት አኳያ በሪፖርቱ በስፋት ተመላክቷል።
በቻይና አፍሪካ የንግድ ምክር ቤት የወጣው ይህ ሪፖርት ለቻይና አፍሪካ መሪዎች እንዲሁም ለኩባንያዎች ቀጣይ አቅጣጫን በተመለከተ 32 ምክረ ሃሳቦችን አካቷል።