ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሴካፋ ዞን የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ ለፍጻሜ ለማለፍ ከዩጋንዳው ሺ ኮርፖሬትስ ጋር ያደርጋል

ነሐሴ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሴካፋ ዞን የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ ለፍጻሜ ለማለፍ ከኡጋንዳው ሺ ኮርፖሬትስ ጋር ዛሬ ጨዋታውን ያደርጋል።

ሁለተኛው የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ በሞሮኮ አስተናጋጅነት በጥር ወር 2015 ዓ.ም ይካሄዳል።

የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት(ሴካፋ) በመወከል በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ በታንዛንያ ከነሐሴ 8 ቀን 2014 ዓ.ም የክለቦች የማጣሪያ ውድድር እየተካሄደ ይገኛል።

በማጣሪያው ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ እየተሳተፈ የሚገኘው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ በአዛም ኮምፕሌክስ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታውን ከኡጋንዳው ሺ ኮርፖሬትስ ከቀኑ 10 ሰአት ላይ ያደርጋል።

በአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው ንግድ ባንክ በምድብ አንድ የዛንዚባሩን ኩዊንስ ዋሪየርስ 9 ለ 0፣የብሩንዲውን ፎፊላ 5 ለ 1 እና የርዋንውን ኤኤስ ኪጋሊ 2 ለ 0 በማሸነፍ በዘጠኝ ነጥብ ከምድቡ አንደኛ ሆኖ ማጠናቀቁ ይታወቃል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በምድብ ጨዋታዎቹ 16 ግቦችን አስቆጥሯል።

የአጥቂ መስመር ተጫዋቿ ሎዛ አበራ በውድድሩ ላይ ዘጠኝ ግቦችን በማስቆጠር የማጣሪያውን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነትን እየመራች ነው።

ሌላኛዋ የንግድ ባንክ የፊት መስመር ተጫዋች መዲና አወል በስድስት ጎል ትከተላለች።

አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ጨዋታውን አስመልክቶ ከሴካፋኦንላይን ጋር ባደረገው ቆይታ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ከምድብ ጨዋታ የተለየ የጨዋታ እቅድ እንደሚያስፈልግና ቡድኑ ለጨዋታው ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

“ለግማሽ ፍጻሜ ያለፈ ማንኛውም ቡድን ክብር መስጠት አለብን፤ተጫዋቾቼ የሚያገኙትን የግብ እድል በሚገባ መጠቀም ይኖርባቸዋል ስንከላከል እንደ ቡድን መሆን አለበት” ብሏል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጋጣሚ ሺ ኮርፖሬትስ በምድብ ሁለት የጅቡቲውን ጋራዴ ሪፐብሊክ 8 ለ 0 እና የደቡብ ሱዳኑን ዬ ጆይንት ስታርርስን 6 ለ 0 ሲያሸንፍ በታንዛንያው ሲምባ ኩዊንስ 2 ለ 0 ተሸንፎ ከምድቡ ሁለተኛ ሆኖ ማለፉ ይታወሳል።

ፒዮና ናቡምባ አምስት እንዲሁም ፌቨር ዳንኤልሊታ ናምባትያ አራት ጎሎችን ለኡጋንዳው ክለብ በውድድሩ ላይ አስቆጥረዋል።የሺ ኮርፖሬትስ አሰልጣኝ ቻርልስ ሉኩላ አዬኮ ንግድ ባንክ ኳስ ረጅም ሰአት ይዞ የሚጫወት ጠንካራ ቡድን ነው ሲል ገልጿል።

“ይህ የጥሎ ማለፍ ውድድር ነው ለፍጻሜው የማለፍ እድል አለን” ብሏል።ሌላኛው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ከምሽቱ 1 ሰአት በአዛም ኮምፕሌኬስ በታንዛንያው ሲምባ ኩዊንስና በርዋንዳው ኤኤስ ኪጋሊ መካከል ይደረጋል።

የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ውድድር ቅዳሜ ነሐሴ 21 ቀን 2014 ዓ.ም ይጠናቀቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም