የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ በማነቃቃት የቀጠናውን ሀገራት ምጣኔ ኃብታዊ ትብብር ያሳድጋል - ኢዜአ አማርኛ
የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ በማነቃቃት የቀጠናውን ሀገራት ምጣኔ ኃብታዊ ትብብር ያሳድጋል
ነሐሴ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ)የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ በማነቃቃት የቀጠናውን ሀገራት ምጣኔ ኃብታዊ ትብብር እንደሚያሳድግ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አብዱላሂ ሲራጅ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ለኢትዮጵያና ለቀጣናው የገቢና ወጪ ንግድ መሳለጥ ትልቅ ሚና ያለውን በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ነሐሴ 8 ቀን 2014 ዓ.ም በይፋ ስራ ማስጀመራቸው ይታወሳል።
አቶ አብዱላሂ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ምርቶችን በጅቡቲ ነፃ የንግድ ቀጠና በኩል ገቢና ወጪ ስታደርግ እንደነበር ጠቁመው፤ የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ ይዞ መምጣቱን አንስተዋል።
ነፃ የንግድ ቀጠናው ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ እቃዎች ምንም አይነት የጉምሩክ ታክስና ሌሎች ስነስርዓቶች ሳይፈጸሙበት አስመጪዎች በቀጥታ ከተመረተበት አገር የሚያስገቡበት የወደብ ቦታ መሆኑን ተናግረዋል።
አገልግሎቱም ሌሎች አገራት ላይ እንዳሉ ወደቦች ሁሉ ለደንበኞች ነፃ የንግድ አገልግሎት የሚሰጥ እንደሆነ ጠቅሰዋል።አስመጪዎች ያስገቡትን ጥሬ እቃም ሆነ ምርት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሚፈልጉበት ቦታም ሆነ ወደ ሌላ ሶስተኛ አገር አጓጉዘው ለመሸጥ እንደሚያስችላቸው ነው ያብራሩት።
በቀጣይም ነጻ የንግድ ቀጠናውን ለማጠናከር ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ሰፊ መሬት በመረከብ የማስፋፊያ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አንስተዋል።
የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና በምስራቅ አፍሪካ ሊተገበር የታሰበውን ነፃ የንግድ እንቅስቃሴ በማገዝ የቀጠናውን ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።
ነጻ የንግድ ቀጠናው ባለሃብቶች ለፋብሪካ ግብዓት የሚፈለጉትን ጥሬ እቃ ከውጭ በማስመጣት በአጠረ ጊዜ ማግኘት እንዲችሉ በማድረግ የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ እንደሚያነቃቃ ጠቁመዋል።
በአውሮፓ፣በእስያ እና በሌሎች ዓለማት ያሉ አስመጪና ላኪዎችም ዕቃዎቻቸውን በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና በማስቀመጥ ይወስድባቸው የነበረን የጊዜ ብክነት እንደሚቀርፍላቸው ገልጸዋል።
በርካታ ኢኮኖሚያዊ እና ቀጠናዊ የጂኦ ፖለቲካ ፋይዳዎች ያሉት የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና፤ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ቀልጣፋ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን ሚናው የላቀ ነው።