የህዳሴ ግድብ ከድህነት የምንወጣበት በመሆኑ የህዝቡ ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል -ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ ከድህነት የምንወጣበት በመሆኑ የህዝቡ ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል -ምሁራን
አርባ ምንጭ ነሐሴ 18/2014 (ኢዜአ) ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ከድህነት መውጫና የአፍሪካም ኩራት በመሆኑ ግንባታውን ከዳር ለማድረስ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ምሁራን አስገነዘቡ፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት ሳይንትፊክ ዳይሬክተር ዶክተር አብደላ ከማል ለኢዜአ እንደገለጹት የህዳሴ ግድብ አገራችን ካለባት የሃይል እጥረትና ከህዝቡ የመብራት ፍላጎት አንፃር ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡
"ኢትዮጵያ በዓለም በድንበር ተሻጋሪ ወንዝ ላይ ግድብ ስትገነባ የመጀመሪያ ሀገር አይደለችም" ያሉት ዶክተር አብደላ አሜሪካ፣ ብራዚል፣ቱርክዬና የመሳሰሉ ሀገራት የዓለም አቀፍ የውሃ ህግ በሚፈቅደው መሠረት ወንዞቻቸውን በመገደብ አገራቸውን ቀይረዋል ነው ያሉት፡፡
በሶስትዮሽ ድርድሩ የኢትዮጵያ አቋም ወጥ እና የማይለዋወጥ በዓለም አቀፍ የውሃ ህግ መርህ ላይ ቆማ ግድብን እየገነባች መሆኑንም በመግለጽ፡፡
የግድቡን ግንባታ ማጠናቀቅ ለኢትዮጵያ የጨለማና ድህነት ማሸነፊያ ወሳኝ መሳሪያ ነው ያሉት ዶክተር አብደላ የግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ ርብርቡ መጠናከር አለበት ብለዋል፡፡
የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም ኩራት ነው ያሉት ምሁሩ በተለይ በመላው አለም የአፍሪካን ገጽታ በመገንባቱ ረገድ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የምታካሂደው የአረንጓዴ አሻራ ደለልን ከመከላከል በላይ ተጨማሪ የውሃ አቅም በማስገኘት ለታችኛውን የተፋሰሱ ሀገራት ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ፕሮጀክቱ መሆኑን ዶክተር አብደላ አመላክተዋል፡፡
የተለያዩ ጫናዎችንና ሴራዎችን በመቋቋም የግድቡን 2ኛ ተርባይን ሃይል ማመንጨት መጀመሩና 3ኛው ዙር ውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ የመብራት ብረሃን ለማያገኘው ህዝብ ትልቅ ተስፋ ነው ብለዋል፡፡
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሃይድሮሊክና የውሃ ሀብት ምህንድስና ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር መልካሙ ተሾመ በበኩላቸው በዓለም ላይ የሃይል አቅርቦት እጥረት ካለባቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡
የህዳሴ ግድብ እየተገነባ ያለው ከደሃው ኪስና በእንጨት ሸክም ጀርባዋ ከጎበጠው እናት ጭምር አስተዋጽኦ በመሆኑ ለኢትዮጵያዊያን ልዩ ትርጉም እንዳለው ጠቅሰው ግድቡን ለማጠናቀቅ መረባረብ አለብን ብለዋል፡፡
የታችኞች ተፋሰስ አገራት በጎርፍ ምክንያት በቢሊየኖች ብር የገነቧቸው የተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ የሚደርሰውን ችግር የህዳሴ ግድብ እስከ 86 በመቶ የደለል ጫናን ከመቀነስ በላይ የሃይል ፍላጎታቸውን እስከ 20 በመቶ የሚያሳድግ በመሆኑ በገንዘብና በሃሳብ ኢትዮጵያን ሊደግፉ ይገባል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የግድቡን ሁለተኛውን ተርባይን ስራ መጀመር ባበሰሩበት ወቅት "ዛሬ ዓባይ ተረት ሳይሆን የሚጨበጥ እውነት ነው፤ ከዘፈን-እንጉርጉሮ ወጥቶ ኢትዮጵያን በብርሃኑ ሊያደምቃት፣ ኃይል ሆኖ ሊያበረታት ከጫፍ ደርሷል፤ በፈጣሪ ርዳታና በኢትዮጵያዊ ወኔ ሙሉ በሙሉ ግንባታውን አጠናቅቀን የልባችን እንደሚሞላ አልጠራጠርም" ማለታቸው ይታወቃል።