ቀጥታ፡

ለህዳሴ ግድብ ግንባታ እየተደረገ ያለው ህዝባዊ ተሳትፎና ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ

ነሐሴ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ)ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እየተደረገ ያለው ህዝባዊ ተሳትፎና ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ልማት ባንክ፣ኢትዮ-ቴሌኮም፣ የአዲስ አበባ ከተማ የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት በጋራ በሰጡት መግለጫ የህዝቡ ተሳትፎ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የግድቡ ግንባታ አሁን ለደረሰበት ስኬት ህዝቡ በሞራል፣በእውቀት፣ በገንዘብና በጉልበት ባደረገው ድጋፍና በመንግስት ቁርጠኝነት ታግዞ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በ11 ዓመታት በነበረው አጠቃላይ የህዝቡ ተሳትፎ 17 ቢሊዮን ብር በቦንድ ግዥና በልገሳ ድጋፍ ስለመደረጉ ተወስቷል።

አርሶ አደርና አርብቶ አደሩ በጉልበቱ የተፋሰስ ልማት ስራ በማከናወን በገንዘብ 121 ሚሊዮን ብር የሚገመት የጉልበት አስተዋጽኦ ማድረጉ ተገልጿል።

ኢትዮጵያ በፍትሀዊ የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመስርታ በአባይ ወንዝ ላይ እያከናወነችው ያለው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በመጪው 2 አመታት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

የግድቡ ግንባታ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ፤ በመግለጫው እንዳሉት ለግንባታው ስኬታማ ሂደት የመንግስትና ህዝቡ የጋራ ጥረት ትልቁን ድርሻ ይይዛል።

የፕሮጀክቱ ግንባታ በበርካታ ተግዳሮቶች አልፎ የተገነባ መሆኑን ጠቅሰው ለማጠናቀቅ የጋራ ትብብራችን ይቀጥል በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

በመሆኑም ለግድቡ ግንባታ ቀደም ሲል ሲደረግ የነበረው ሁሉን አቀፍ ድጋፍና ትብብር እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ፤የግድቡ ግንባታ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ባንኩ የፋይናንስ ምንጭ መሆኑን ይቀጥላል ብለዋል።

May be an image of 1 person

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የኮሙኒኬሽን ሃላፊ አቶ ሀይሉ አብርሃም፤የሁለተኛውን ተርባይን ኃይል የማመንጨትና 3ኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ ትልቅ መነሳሳት የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም በቀጣይነት የድጋፍና ትብብር ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮ ቴሌኮም በኩል በ''8100A'' አጭር የጽሁፍ መልእከት የሚደረገው ተሳትፎም እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በቦንድ ግዥ ሂደት የልማት ባንክ ሚና የላቀ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን በቀጣይም ተመሳሳይ ተግባራት እንዲቀጥሉ በመግለጫው ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም