ቀጥታ፡

በላልይበላና አካባቢው የልማትና የቱሪዝም እንቅስቃሴ ዙሪያ የሚመክር የህዝብ መድረክ እየተካሄደ ነው

ነሐሴ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ)የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ የሚመሩት በላልይበላና አካባቢው የልማትና የቱሪዝም እንቅስቃሴ ዙሪያ የሚመክር የህዝብ መድረክ በከተማዋ መካሄድ ጀመረ።

በመድረኩ የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናኒሴ ጫሊን ጨምሮ የፌደራልና የክልል አመራሮችና የላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች እየተሳተፉ ይገኛል።

በውይይት መድረኩም የላልይበላ ከተማ ጥንታዊ ታሪክና አሁናዊ ችግር ዙሪያ ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቧል።

ጥናታዊ ፅሁፉን ያቀረቡት ቀሲስ ይሄነው መልኩ እንዳሉት ላስታ ላልሊበላ በቀደሙት ዘመናት የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና ያገለገለች ጥንታዊና ታሪካዊ ከተማ ናት።

የላስታ ላልይበላ ለሃገረ መንግስት ምስረታና ኢትዮጵያ በአለም አቀፉ መድረክ የጎላ እውቅና እንዲኖራት ላልይበላ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ገልፀዋል።

በላልይበላ ከ20 በላይ ከአለት የተፈለፈሉና በዋሻ ውስጥ የተሰሩ አብያተ ክርስትያናት እንዳሉ ጠቅሰው፤ እንደ አሸንድየ አይነት ደግሞ 13 አይነት ባህል ባለቤት መሆኗን አመላክተዋል።

ይሁን እንጅ ላልይበላ ከተማ እንደ ታሪካዊና ጥንታዊ ከተማነቷ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ የሚመጣጠን የመሰረተ ልማት ዝርጋታ አለመኖሩን ገልፀዋል።

ላልይበላ ከተማ አሁንም የመብራት ፣ውሃና መንገድ መሰረተ ልማት ችግር አሉባት ያሉት ቀሲስ ይሄነው የውቅር አብያተ ክርስትያናትም የከፋ ጉዳት እያጋጠማቸው መሆኑን በጥናታዊ ፅሁፋቸው አመላክተዋል።

የላልይበላ ከተማ የቱሪዝም ማእከል እንዳትሆን የተሰጣት የከተማነት መዋቅር ደረጃ ማነቆ መሆኑንም አስታውቀዋል።በመሆንም የክልሉና የፌደራል መንግስቱ ለቱሪዝም ሃብቱ ትልቅ ትኩረት የሰጠ በመሆኑ የላልይበላ ከተማን የረዥም ጊዜ ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጡበትም ጠይቀዋል።

ላልይበላ ከተማ የኮሮና ቫይረስ መከሰትና የህወሃት የሽብር ቡድን ወረራ ምክንያትም በቱሪዝም ዘርፉ ተሰማርተው የነበሩ ከ7 ሺህ 300 በላይ ዜጎች ከስራ ውጭ መሆናቸው ተመላክቷል።

ሆቴሎችና አስጎብኝዎችም ከስራ ውጭ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የአካባቢው የቱሪዝም ፍሰት ወደ ቀደመ እንቅስቃሴው እንዲመለስ መንግስት ከፍተኛ እገዛ ማድረግ እንዳለበትም ጠይቀዋል።

ለቀረቡት የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ፤ የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናኒሴ ጫሊና በሌሎች ባለድርሻ አካላት ምላሽና ማብራሪያ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም