ቀጥታ፡

አገራዊ ምክክሩ ተዓማኒ፣ ግልጽና አሳታፊ ሆኖ እንዲካሄድ የድርሻችንን እንወጣለን-ምክር ቤቶቹ

ነሐሴ 17 ቀን 2014(ኢዜአ) አገራዊ ምክክሩ ተዓማኒ፣ ግልጽና አሳታፊ ሆኖ እንዲካሄድ የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጹ፡፡

ሁለቱም ምክር ቤቶች በአገራዊ የምክክር ሂደቱ ላይ የበኩላቸውን መወጣት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡

May be an image of 10 people, people standing and indoor

በአገራዊ ጉዳይ ላይ በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረሙ ወዲህ ውይይቱ የመጀመሪያው መሆኑም ተገልጿል፡፡

በውይይቱም አገራዊ ምክክሩ በስኬት ተጠናቆ የታለመው አገራዊ መግባባት እውን እንዲሆን የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የአገራዊ ምክክሩ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለስኬታማነቱ የሁሉም ማኅበረሰብ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ሄኖክ መለስ፤ የምክክሩ ዋና ዓላማ አገራዊ መግባባትን መፍጠር በመሆኑ ሁለቱም ምክር ቤቶች ለስኬታማነቱ የበኩላቸውን ይወጣሉ ብለዋል።

የምክክር ሂደቱም አሳታፊ፣ ግልጽ እና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

May be an image of 1 person

የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር ራሄል ባፌ፤ ሁለቱ ምክር ቤቶች ለአገር ጠቀሜታ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ያደረጉት ጥምረት ዘላቂ እንዲሆን ሥራዎች የሚከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

አገራዊ ምክክሩም የታለመለትን ግብ እንዲመታ ምክር ቤቱ የሚጠበቅበትን ለመወጣት ይንቀሳቀሳል ብለዋል።

በብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማኅበራት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ዓለሙ ስሜ፤ ሁለቱም ምክር ቤቶች ለአገራዊ ምክክሩ ትኩረት መስጠታቸው ለሂደቱ ስኬታማነት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

May be an image of 1 person and suit

አገራዊ ምክክሩ የነገዋን ኢትዮጵያ ዕጣ-ፈንታ የሚወስንና ለትውልድ የተሻለች አገር ለማሳለፍ ሚናው ከፍተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የአገራዊ ምክክር ምክትል ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ፤ ሁለቱ ምክር ቤቶች አገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን ሕዝቡን በማስተማርና ሃሳቡን ከማስረጽ አንጻር ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም በአጀንዳ፣ በተሳታፊ፣ በአወያይ፣ በምክክር መሪዎች መረጣ እና ሌሎችም አስፈላጊ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ ትብብርና እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በመድረኩ የተገኙት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፤ ኢትዮጵያን ወደ ፊት ለማሻገር ሁለቱም ምክር ቤቶች የፈጠሩት ጥምረት ይበል የሚያሰኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በውይይቱ የሁለቱ ምክር ቤቶች ተወካዮች፣ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች እንግዶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም