የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በበጀት ዓመቱ 51 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በበጀት ዓመቱ 51 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን ገለጸ
ነሐሴ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ)በ2014 በጀት ዓመት 51 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በመሰብሰብ ከፍተኛ ገቢ ማስመዝገቡን የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አስታውቋል።
ድርጅቱ 7 ነጥብ 2 ሚሊየን ቶን የተለያየ የደረቅ ጭነት አገልግሎቶችን መስጠቱም ተገልጿል።
የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሮባ መገርሳ፤ተቋማቸው በ2014 በጀት ዓመት ከፕሮጀክቶች አፈፃጸም፣ከገቢ አሰባሰብና ሌሎች ጉዳዮችን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ባለፈው በጀት ዓመት የወደብ አሰራር፣የሩስያና ዩክሬን ግጭት፣የምግብ ምርት ዋጋ ንረት፣ የኮቪድ ወረርሽኝ በባህር ንግድ ዘርፉ ላይ ዓለም አቀፍ የንግድ መዛባት ማስከተላቸውን ጠቁመዋል።
ኤቨርግሪን መርከብ የስዊዝ ቦይን መዝጋቷን ተከትሎ የንግድ እንቅስቃሴውን በማስተጓጎል በዓለም አቀፍ ደረጃ እስከ 28 ቢሊየን ዶላር የካሳ ክፍያ ማስከተሉን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የወደቦች መጨናነቅ፣የኮንቴነር እጥረት፣ የእቃ መጫኛ ዋጋ መናርን ጨምሮ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ታይቶ የማይታወቅ የንግድ መዛባት መከሰቱን አንስተዋል።
በተለይም በአፈር ማዳበሪያ፣በብረት፣ በነዳጅ፣ በስንዴ፣ በበቆሎ፣ በሱፍ ዘይት እና በሌሎች ምርቶች የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ የንግድ መዛባትና የጭነት መስተጓጎል መከሰቱን አስታውሰዋል።
ድርጅቱ ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘበ ዕቅድ በማውጣት በ2014 በጀት ዓመት 7 ነጥብ 2ሚሊየን ቶን የደረቅ ጭነት አገልግሎት መስጠቱን ጠቅሰዋል።
በዚህም የእቃ ጭነት፣የባህርና የየብስ የዕቃ ማስተላለፍ፣ የመርከብ ውክልና፣የወደብና ተርሚናል የጭነት አገልግሎቶች በድርጅቱ ተሰጥተዋል ብለዋል።
በአገልግሎቱ የብረት፣የአፈር ማዳበሪያና ሌሎች ምርቶችን ማጓጓዝ እንደተቻለ ጠቁመዋል።
በዚህም የባለፈው ዓመት ተጨማሪ የዩሪያ ግዥን ጨምሮ 14 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያን በመርከቦች ወደ ወደብ በማምጣት በባቡርና በከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎች ለአርሶ አደሩ ማሰራጨት መቻሉን ገልጸዋል።
ድርጅቱ በሰጣቸው የጭነት አገልግሎቶች 51 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን ገልጸው፤በበጀት ዓመቱ የድርጅቱን የፋይናንስ አቅም 64 ነጥብ 85 ቢሊየን ብር ማድረስ እንደተቻለም ጠቁመዋል።
የሞጆ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያና መሰረተ ልማት ግንባታን ጨምሮ ለረዥም ዓመታት ሲጓተቱ የነበሩ የወደብ ልማት፣የህንፃ ግንባታና ሌሎች ፕሮጀክቶች ላይ በበጀት ዓመቱ የተሳካ ስራ መሰራቱን አንስተዋል።
በመርከቦች ላይ የነበረን የብድር ዕዳ በማጠናቀቅም የመርከቦችን የጭነት አገልግሎት ወደ ትርፋማነት በማሸጋገር 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ትርፍ እንዲያስመዘግቡ መደረጉን ተናግረዋል።
ማህበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት በተከናወነ ተግባርም ለአገር መከላከያ ሠራዊት እንዲሁም በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ሰለባ ለሆኑ ወገኖች ከ161 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን አመላክተዋል።
የድርጅቱ አጠቃላይ የዕቅድ አፈጻጸም 92 በመቶ መሳካቱንም ዋና ስራ አስፈጻሚው በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል።