ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያንን ከድህነት የሚያላቅቅ ነው--በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያንን ከድህነት የሚያላቅቅ ነው--በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር
ነሃሴ 17/2014/ኢዜአ/ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያንን ከድህነት የሚያላቅቅ መሆኑን በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ ገለጹ።
ግድቡ የልማት፣የትብብርና የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክት መሆኑንም አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በበይነ መረብ ቆይታ ያደረጉት አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ እንዳሉት ግድቡ የአየር ፀባይ ለውጥን ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ የታዳሽ ኃይል ምንጭ በመሆን ያገለግላል፡፡
ግድቡ ለሀገሪቱ ልማትና ዕድገት ዋነኛ መሰረት የሆነውን የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት በአገሪቱ መፃኢ ዕድል ላይ ዘርፈ ብዙ አስተዋፅኦ እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይሉን ለጎረቤት ሀገራት በመሸጥ የውጭ ምንዛሪ እንደምታገኝበት በመጠቆም ትስስሩ በሀገራቱ መካከል ያለውን አብሮነት ያጠናክረዋል ብለዋል፡፡
"ከሁሉ በላይ የፕሮጀክቱ እውን መሆን ኢትዮጵያውያንን ከድህነት በማላቀቅ በጨለማ ወስጥ ለሚኖሩ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች ብርሃን እንደሚሰጥ" ነው ያብራሩት፡፡
ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች በሀገሪቱ ለሚገነቡ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ገንዘብን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከዚህም ባለፈ በሀገሪቱ የዕድገትና የመረጋጋት ጉዞ ላይ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን አምባሳደር ሄኖክ ጠቁመዋል፡፡
"በፈረንሳይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ከዚህ በፊት ከነበረው በላቀ መንፈስ በጋራ በመንቀሳቀስ የግድቡን ግንባታ እየደገፉ ነው” ብለዋል፡፡
የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር ሙሌት በስኬት መጠናቀቁና የሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ዳያስፖራው ደጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል የበለጠ መነሳሳትን ፈጥሯል ነው ያሉት።
የግድቡ መካከለኛ ክፍል ቁመት አሁን ላይ ከባህር ጠለል በላይ 600 ሜትር መድረሱ የተገለጸ ሲሆን የግራና ቀኝ ክፍሉ ደግሞ 611 ሜትር ደርሷል፡፡
ኃይል ማመንጨት የጀመሩት ሁለቱ ተርባይኖች በሙሉ አቅማቸው ኃይል ሲያመነጩ 750 ሜጋ ዋት ኃይል የሚሰጡ ሲሆን አሁን ላይ 550 ሜጋ ዋት ኃይል እያመነጩ መሆኑን የግድቡ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡