ቀጥታ፡

በአንድ እጃችን አሸባሪውን አልሸባብ እየተዋጋን በሌላ እጃችን የልማት እቅዶቻችንን ለማሳካት እንሰራለን - የሶማሌ ክልል ሸበሌ ዞን አስተዳደር

ነሐሴ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ድንበር በመሻገር ጥፋት ለመፈፀም እየጣረ ያለውን የአልሸባብ የሽብር ቡድን በአንድ እጃችን እየተዋጋን በሌላ እጃችን የልማት እቅዶቻችንን ለማሳካት እንሰራለን ሲሉ በሶማሌ ክልል የሸበሌ ዞን አስተዳዳሪ አደም መሐመድ ተናገሩ።

አቶ አደም ወቅታዊ የዞኑን የፀጥታና የልማት እንቅስቃሴዎች በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ አሸባሪው አልሸባብ በዞኑ ፌርፌር እና የድ በተባሉ አካባቢዎች የጥቃት ሙከራ አድርጎ እንደነበር አስታውሰዋል።

ሆኖም የአሸባሪ ቡድኑ ሙከራ በአገር መከላከያ ሠራዊትና በክልሉ የጸጥታ ኃይል የተቀናጀ እርምጃ የሽብር ቡድኑ አባላት መደምሰሳቸውንና በርካቶችም በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልፀዋል።

ድንበር በመሻገር ሰርጎ ለመግባት የሞከረው የሽብር ቡድኑ የማያዳግም እርምጃ ተወስዶበት ከፍተኛ ኪሳራ የደረሰበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለዚህ ድል መገኘት የሸበሌ ዞን ሕዝብ ከጸጥታ ኃይሉ ጎን በመሰለፍ የነበረው ተሳትፎ አይተኬ ሚና እንደነበረው አስታውሰዋል።

ለሠራዊቱ ሁለንተናዊ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር የሽብር ቡድኑን ሰርጎ ገቦች በማጋለጥና በቀጥታ በመዋጋት ጭምር የጀግንነት ገድል መፈጸማቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በዞኑ አንጻራዊ ሰላም መፈጠሩን ገልጸው፤ ሕዝብን ያሳተፈ የሰላምና ጸጥታ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የሸበሌ ዞን ከሶማሊያ ሦስት ክልሎች ጋር የሚዋሰን በመሆኑ አልሸባብ ዳግም ትንኮሳ እንዳይፈጽም የተቀናጀ የጸጥታ ጥበቃ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያን ድንበር በመሻገር ጥፋት ለመፈጸም እየጣረ ያለውን የአልሸባብ የሽብር ቡድን በአንድ እጃችን እየተዋጋን በሌላ እጃችን የልማት እቅዶቻችንን ለማሳካት እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

ከሐምሌ 14 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በሶማሌ ክልል ጠረፋማ አካባቢዎች ወደ ኢትዮጵያ ሰርጎ ለመግባት በሞከረው የአልሸባብ የሽብር ቡድን ላይ በተወሰደ የተቀናጀ እርምጃ 24 አመራሮቹን ጨምር 813 የሽብር ቡድኑ አባላት መደምሰሳቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም