በበጀት ዓመቱ 7 ነጥብ 2 ሚሊየን ቶን የደረቅ ጭነት አገልግሎት መስጠት ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በበጀት ዓመቱ 7 ነጥብ 2 ሚሊየን ቶን የደረቅ ጭነት አገልግሎት መስጠት ተችሏል
ነሃሴ 17/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በ2014 በጀት ዓመት 7 ነጥብ 2ሚሊየን ቶን የደረቅ ጭነት አገልግሎት መስጠቱን አስታወቀ።
የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሮባ መገርሳ፤ ተቋማቸው በ2014 የበጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀምን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በበጀት ዓመቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነትና ሌሎች ምክንያቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ የንግድ መዛባት ማስከተላቸውን ጠቁመዋል።
በተለይም በአፈር ማዳበሪያ፣ በብረት፣ በነዳጅ፣ በስንዴ፣ በበቆሎ፣ በሱፍ ዘይት እና በሌሎች የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ የንግድ መዛባትና መስተጓጎል መከሰቱን አስታውሰዋል።
በዚህም ውስጥ ሆኖ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በሺፒንግ፣ በወደብና ሌሎች መሰል አገልግሎቶች በበጀት ዓመቱ 7 ነጥብ 2 ሚሊየን ቶን የደረቅ ጭነት አገልግሎት መሰጠቱን አስታውቀዋል።
የጭነት አገልግሎቱም በዋናነት በጅቡቲ ወደብ የተሰጠ መሆኑን ጠቅሰው የድርጅቱ ዕቅድ አፈጻጸምም 92 በመቶ መሳካቱን ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው ያብራሩት።