ቀጥታ፡

ምክር ቤቶቹ በአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ላይ የበኩላቸውን ሚና መወጣት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ እየመከሩ ነው

ነሃሴ 17/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ላይ የበኩላቸውን መወጣት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ እየመከሩ ነው።

ውይይቱ ምክር ቤቶቹ በአገራዊ ጉዳይ ላይ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረሙ ወዲህ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።

በውይይቱ ላይ እንደተጠቆመውም ሁለቱ ምክር ቤቶች በአገራዊ ጥቅም ላይ በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ ናቸው።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ሄኖክ መለስ እንዳሉት፤ የአገራዊ ምክክሩ ዋና ዓላማ አገራዊ መግባባትን መፍጠር በመሆኑ ሁለቱም ምክር ቤቶች ለስኬታማነቱ የበኩላቸውን ይወጣሉ።

የአገራዊ ምክክር ሂደቱም አሳታፊ፣ ግልጽ እና ነጻ እንዲሆንም የሚጠበቅባቸውን የሚወጡ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር ራሄል ባፌ በበኩላቸው ሁለቱ ምክር ቤቶች ለአገር ጠቀሜታ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ያደረጉት ጥምረት ዘላቂ እንዲሆን ስራዎች የሚከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

አገራዊ ምክክሩም የታለመለትን ግብ እንዲመታ ምክር ቤቱ የሚጠበቅበትን ለመወጣት ይንቀሳቀሳል ብለዋል።

በውይይቱ በብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማኅበራት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ዓለሙ ስሜ፣ የሁለቱ ምክር ቤቶች ተወካዮች፣ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም