በአሜሪካ በአንድ ምሽት ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ከ70 ሺህ ዶላር በላይ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በአሜሪካ በአንድ ምሽት ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ከ70 ሺህ ዶላር በላይ ተሰበሰበ
ነሐሴ 17 ቀን 2014(ኢዜአ) በአሜሪካ ዋሸንግተን ዲሲ በአንድ ምሽት በተካሄደ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐግብር ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚውል ከ70 ሺህ ዶላር በላይ ተሰበሰበ።
ለሕዳሴ ግድብ ድጋፍ ማሰባሰቢያ በተዘጋጀው “ማይ ገርድ ዶት ኮም” (www.mygerd.com) ድረ-ገጽ የተሰበሰበው 310 ሺህ ዶላርም ለመንግስት ገቢ ተደርጓል።
“ደርሰናል እናጠናቅቀዋለን” በሚል መሪ ሀሳብ በዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተዘጋጀው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የገቢ ማሰባሰቢያና የምስጋና መርሐግብር በአካልና በበይነ መረብ በማቀላቀል(ሀይብሪድ) ተካሄዷል።
በዚህ ወቅት በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ለሕዳሴ ግድብ በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በውግንና(አድቮኬሲ)፣በማህበራዊ ትስስር ገጾች ቅስቀሳ፣በምርምርና በተለያዩ መስኮች እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል።
“የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአንድነታችን ድንቅ ማሳያና ለልማት ያለንን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነው” ያሉት አምባሳደሩ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሶስተኛውን ዙር የግድቡ የውሃ ሙሌት በመጠናቀቁና ሁለተኛው ተርባይን ሃይል ማመንጨት በመጀመሩ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ሁሉም አካል የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድጋፍ ማድረጉን መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በበኩላቸው የሕዳሴ ግድብን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ የኢትዮጵያን የለውጥና እድገት ሕልሞች እውን ለማድረግ ልናውለው ይገባል ብለዋል።
የገቢ ማሰባሰቢያና የምስጋና መርሐግብር ተሳታፊዎች ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በሁሉም መስኮች ድጋፋቸውን ማድረግ እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
በመርሐግብሩ ላይ በአካልና በይነ መረብ ከ200 በላይ ሰዎች መሳተፋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በዋሺንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐግብር ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚውል ከ70 ሺህ ዶላር በላይ ገንዘብ ተሰብስቧል።
ለሕዳሴ ግድብ ድጋፍ ማሰባሰቢያ በተዘጋጀው “ማይ ገርድ ዶት ኮም” ( www.mygerd.com) ድረ-ገጽ የተሰበሰበው 310 ሺህ ዶላር ለመንግስት ገቢ ተደርጓል።
“ማይ ገርድ ዶት ኮም” ሐምሌ 13 /2013 ዓ.ም ይፋ የተደረገ የበይነ መረብ አማራጭ ሲሆን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ለሕዳሴ ግድቡ ድጋፍ የሚያደርጉበት ነው።
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በድረ-ገጹ 313 ሺህ 771 ገቢ ለግድቡ ተሰብስቧል።