በክልሉ በሚተከሉ ችግኞች የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው- ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በሚተከሉ ችግኞች የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው- ቢሮው
ሚዛን አማን ፣ ነሀሴ 16/2014 (ኢዜአ) ለአካባቢ ጥበቃ በሚተከሉ ችግኞች አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት መደረጉን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ደን፣ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ ዶክተር አሥራት ገብረማርያም ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ ያለውን ሰፊ የደን ሽፋን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ተጨማሪ ችግኞች እየተተከሉ ነው።
ዘንድሮ ከ121 ሚሊዮን በላይ የተለያየ አገልግሎት ያላቸውን ችግኞች መዘጋጀታቸውንና እስካሁንም በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ከ100 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት መተከላቸውን ገልጸዋል።
ከክልሉ የአየር ጸባይ ተስማሚነት አንጻር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ እስከ መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ እንደሚቀጥልም ዶክተር አሥራት አመልክተዋል።
እንደ ሃላፊው ገለጻ፣ የተተከሉ ችግኞች የጽድቀት መጠናቸውን ለማሳደግ ክትትል እየተደረገ ነው።
የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች በብዛት በመትከል በደን ላይ ጥገኛ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ እየተሰራ መሆኑንም ዶክተር አስራት ተናግረዋል።
"ለአብነትም ማንጎ፣ ፓፓያ፣ ቡና፣ አቡካዶና የቀርቀሃ ምርቶችን ለማስፋፋት በታሰበው መሰረት ችግኞች ተዘጋጅተው ወደ ተከላ ሥራ ተገብቷል" ብለዋል።
በማኅበረሰቡ ባህል እስካሁን ተጠብቆ የቆየው የክልሉ የደን ሀብት ሳይወድም ለማቆየትና ህብረተሰቡም ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ከደኑ እንዲጠቀም ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራም ነው ያስታወቁት።
በክልሉ ያለውን የደን አጠባበቅ ባህል ማዳበር ላይ ቢሮው የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣም አረጋግጠዋል።
"ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት በአሳታፊ ደን አጠባበቅ ሥርዓት ደንን በመጠበቅ የተሻለ መጠቀም የሚያስችሉ አማራጮችን እናስፋፋለን" ብለዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በበኩላቸው በክልሉ ሰፊ የደን ሀብት ቢኖርም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በርካታ ችግኞችን የመትከል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በዓመቱ ለመትከል በዕቅድ ከተያዘው የችግኝ መጠን እስካሁን ድረስ 80 በመቶ የሚሆነው መተከሉንና የተተከሉትም የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የክልሉ ማህበረሰቡ ጠብቆ ያቆየውን የተፈጥሮ ሀብት ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
"በተለይ ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በማሳደግ የአርሶ አደሩን ኑሮ ወደ ተሻለ ከፍ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመናበብ ይሰራል" ብለዋል።
በኢትዮጵያ በባዮስፌር ከተመዘገቡ አራት እምቅ የተፈጥሮ ደኖች መካከል ሁለቱ በክልሉ ካፋ እና ሸካ ዞን እንደሚገኙ አቶ ማስረሻ አስታውቀዋል።
በክልሉ ካፋ ዞን ጠሎ ወረዳ የሚኖሩት አቶ አድማሱ አስፋው የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው፣ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ማንጎ፣ አቡካዶ እና መሰል የፍራፍሬ ችግኞችን አዘጋጅተው በመትከል ተጠቃሚ ለመሆን እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ከመትከል ባለፈ ችግኞችን ከእንስሳት ንኪኪ ነጻ ለማድረግና ለፍሬ ለማብቃት ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ እንደሚያደርጉም አመልክተዋል።
ለቤት መስሪያነት እንጨት መቁረጥን ለማስቀረትም በጓሯቸው ቀርቀሃ እና መሰል የችግኝ አይነቶችን መትከላቸውን ገልጸዋል።