በድሬዳዋ ከአምስት ሺ በላይ ከፍለው መታከም የማይችሉ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው "በጎነት ለጤናችን"ሳምንታዊ የጤና ዘመቻ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ ከአምስት ሺ በላይ ከፍለው መታከም የማይችሉ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው "በጎነት ለጤናችን"ሳምንታዊ የጤና ዘመቻ እየተካሄደ ነው
ነሐሴ 16 ቀን 2014(ኢዜአ) ከአምስት ሺ በላይ ከፍለው መታከም የማይችሉ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የህክምና ዘመቻ እና ከመቶ በላይ አዛውንቶች የማዕድ ተጋሪ የሚያደርገው "በጎነት ለጤናችን"ሣምንታዊ ዘመቻ ዛሬ በድሬዳዋ ተጀመረ።
የጤና ምርመራ በማድረግ ዘመቻውን ያስጀመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከዲር ጁሃር ከህክምና አገልግሎቱ በተጨማሪ በዘመቻው አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ቤቶች ይታደሳሉ ብለዋል።
በጎነት ለጤንነት በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በአገር አቀፍ ደረጃ ለአንድ ሳምንት የሚካሄደውን እና ከመቶ ሺ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው ዘመቻ ዛሬ በሁሉም ክልሎች እና ከተሞች ተጀምሯል።
ከንቲባ ከዲር ጁሃር እንዳሉት፤ዘመቻው በመተባበር እና በመረዳዳት ሁሉም አቀበቶች በስኬት መውጣት እንደሚቻል ማሳያ ነው።
ዳዊት የጤና ፋውንዴሽን እና የግል የጤና ተቋማት ለዘመቻው መሳካት በገንዘብ ፣ በመድኃኒት እና በሰው ኃይል ያደረጉት ድጋፍ የሚመሰገን እና የሚበረታታ ነው ብለዋል።
መንግስት፣ ባለሃብቶች እና ህብረተሰቡ በመቀናጀት የጀመሩትን ሁሉን አቀፍ የለውጥ ጉዞ በስኬት ለመደምደም መረባረቡ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል ።
"ለዘመቻው በተመቻቸው ስፍራ ላይ ህብረተሰቡ መሳተፍ እና ደም በመለገስ የወላድ እናቶችን ህይወት እንዲታደግ ጥሪ አቀርባለሁ" ብለዋል።
የጤና ሙያ መሠረት እና እርካታ በጎነት ነው ያሉት ደግሞ የጤና ባለሙያዋ እና የጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ለምለም በዛብህ ናቸው።
በሶስት ዋና ዋና የድሬዳዋ አደባባዮች እየተካሄደ የሚገኘው የነፃ የህክምና ምርመራ እና ህክምና በጎዳና ላይ የሚገኙትን ጨምሮ ከአምስት ሺ በላይ ከፍለው መታከም የማይችሉ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።
በተጨማሪም በሳምንቱ ዘመቻ ለመቶ ችግረኞች ቤተሰቦች ማዕድ ከማጋራት ባሻገር በክረምቱ ቤታቸው የፈረሰባቸው የተመረጡ ሰዎች ቤቶች ይጠገናሉ ብለዋል።
የህክምናው ተጠቃሚ አቶ ጣሰኝ ሙላቱ ለአርባ አመታት ወደ ህክምና ተቋማት ሄደው እንደማያውቁ ገልፀው ዛሬ ለደሃው የተዘጋጀው በረከት ወደፊትም መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።
ሌላው የህክምናው ተጠቃሚ አቶ አብዱልቃሲም አብዱልሰመድ በበኩላቸው ይህ የተቀደሰ የክረምት ስራ በበጋው ቢጠናከር የበርካታ ወገኖችን ህይወት መታደግ እንደሚቻል ተናግረዋል።