ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ የንግድ ማጭበርበርና ኮንትሮባንድን ለመከላከል ባደረገው ዘመቻ ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ማዳን ችሏል

ሀዋሳ፣ ነሐሴ 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ንግድ ማጭበርበርና ኮንትሮባንድን ለመከላከል ባደረገው ዘመቻ አገር ልታጣ የነበረውን ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ማዳን መቻሉን አስታወቀ።

የኮሚሽኑን የ2014 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2015 በጀት ዓመት እቅድ ላይ የሚመክር መድረክ ዛሬ በሐዋሳ ከተማ ተጀምሯል።

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙሌ አብዲሳ እንዳስታወቁት ኮሚሽኑ የቀረጥና ታክስ ገቢን በብቃት ከመሰብሰብ፣ ኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድን ከመከላከልና ከመቆጣጠር ባለፈ የሀገሪቱ የውጭ እና የገቢ ንግድ እንቅስቃሴ እንዲያድግ የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

በ2014 በጀት ዓመት 154 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ140 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ጠቁመዋል።

ይህም አፈጻጸም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተሰበሰበው ብር ጋር ሲነፃፀር በ28 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብልጫ ማሳየቱን ጠቁመዋል።

ይህም ዘመናዊ የጉምሩክ አስተዳደር ሥርዓት በመዘርጋትና ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት የወጪና ገቢ ንግድ እንቅስቃሴን በማሳለጥ የተገኘ ስኬት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኮሚሽኑ በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም ንግድ ማጭበርበርና ኮንትሮባንድን ለመከላከል በየደረጃው ባደረገው ዘመቻ አገር ልታጣ የነበረውን 50 ቢሊዮን ብር መዳን መቻሉን ገልፀዋል።

መንግሥት የሀገር ውሰጥ ኢንቬስትመንትን ለማበረታታት ባስቀመጠው የህግ ማእቀፍ መሰረት ከ89 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ እቃዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ መደረጉን አስታውቀዋል።

በተለይ ሀገራዊ የሎጂስቲክስ ማነቆዎች እንዲፈቱ በተደረገው እንቅስቃሴም በርካታ ስኬቶች መገኘታቸውን ነው ያመላከቱት።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የሞጆ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌቱ አለሙ በሰጡት አስተያየት በሀገሪቱ በመልቲ ሞዳል ሥርዓት ከሚጓጓዙ 80 በመቶ እቃዎች የሚስተናገዱት በሞጆ ጉምሩክ ነው።

ከዚህ አኳያ ቅርንጫፉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አገልግሎትን በተሳለጠ መንገድ በማከናወን በገቢና ወጪ እቃዎች ላይ ከሚጣል ቀረጥና ታክስ ገቢን በላቀ ደረጃ በመሰብሰብ ስኬታማ መሆኑን ተናግረዋል።በዚህ ረገድ በ2014 በጀት ዓመት 52 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 99 ነጥብ 6 በመቶ ማሳካት መቻሉን አውስተዋል።

የተገኘው ውጤት ዘንድሮ ሀገራችን በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ተግዳራቶች ስትፈተን በነበረበት ወቅት በመሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ጠቅሰው የተመዘገበው ስኬትም ለ2015 በጀት ዓመት እንደ ግብዓት በመውሰድ የተሻለ ስራ ለመስራት ያተጋናል ብለዋል።

ለአራት ቀናት በተዘጋጀው በዚሁ መድረክ ላይ በቅርቡ የተሾሙትን የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ ዓይናለም ንጉሴን ጨምሮ የኮሚሽኑ ከፍተኛ አመራሮች፣ የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም