የቤንች ማጂ ቡና እግር ኳስ ክለብ የተሻለ ተወዳዳሪ እንዲሆን ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል---የስፖርቱ ቤተሰቦች - ኢዜአ አማርኛ
የቤንች ማጂ ቡና እግር ኳስ ክለብ የተሻለ ተወዳዳሪ እንዲሆን ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል---የስፖርቱ ቤተሰቦች
ሚዛን መስከረም 8/2011 የቤንች ማጂ ቡና እግር ኳስ ክለብ የተሻለ ተወዳዳሪ እንዲሆን ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባ የስፖርት ቤተሰቦች ገለፁ። ክለቡ በ2010 የውድድር ዓመት ያሳየውን ጠንካራ አጨራረስ አስመልክቶ ለቡድኑ አባላት የምስጋና መርሀ ግብር ተካሂዷል። ከክለቡ ደጋፊዎች መካከልም አቶ ዋለልኝ ቸርነት እንዳሉት ክለቡ በመጀመሪያ ዓመት ቆይታው ያሳየው ውድድር የሚበረታታ ነው። "በተያዘው 2011 የውድድር አመት ጥሩ ተወዳዳሪ በመሆን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን መቀላቀል እንዲችል ብቃት ያላቸው አዳዲስ ተጫዋቾችን ማካተት አለበት " ብለዋል ። ሌላው የክለቡ ደጋፊ አቶ ኬራ ባልኩ በበኩላችው ክለቡ የተደራጀና ጠንካራ ደጋፊ አባላትን ማፍራት ላይ በትኩረት መሰራት እንደሚገባው ጠቁመዋል። "አመቺ የልምምድና የመጫወቻ ሜዳ እንዲኖረው ከወዲሁ ሊሰራ ይገባል" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ። የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ወንዳየሁ ኪዳኔ ክለቡ በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ ተደጋጋሚ ሽንፈት በማስተናገዱ ውጤት ርቆት የነበረ ቢሆንም መሠረታዊ ለውጦችን በማድረግ ከመውረድ ስጋት ወጥቶ ደረጃውን ማሻሻሉን ገልጸዋል። "በተያዘው 2011 የውድድር አመት የኢትዮጵያ ፕሪሜርሊግን መቀላቀል እንዲችል በተሻለ ዝግጅት ይቀርባል" ብለዋል። የክለቡ ፕሬዝደንት አቶ ዳዊት ገሙ በበኩላችው ክለቡ የተሻለ ደረጃ እንዲደርስና ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሜርሊግ ማደግ እንዲችል የሚመለከታቸውን ሁሉ ድጋፍ እደሚፈልግ ተናግረዋል። እንደ አቶ ዳዊት ገለጻ የክለቡን የበጀት አቅም በማሳደግ መሠረታዊ ፍላጎቶቹን ማሟላት የ2011 ውድድር ዓመት ቀዳሚ ተግባር ነው። በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ሁለተኛ ዙር ላይ አሰልጣኙን ጨምሮ በርካታ ተጫዋቾች መሰናበታቸውንና በምትካቸው ስምንት አዳዲስ ተጫዋቾችን ማስፈረም መቻሉን አቶ ዳዊት ተናግረዋል። "በዚህም ክለቡ ከነበረበት የመውረድ ስጋት በመውጣትና ደረጃውን በማሻሻል 10ኛ ደረጃ ላይ ሆኖ የውድድር ዓመቱን እንዲያጠናቅቅ አስችሎታል" ብለዋል ።