ቀጥታ፡

መንግስት ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል--ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን

ሰቆጣ ፣ነሀሴ 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መንግስት ችግሮችን በውይይትና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን በድምቀት እየተከበረ በሚገኘው የሻደይ በዓል ላይ ተገኝተዋል።

መንግስት ከህወሃት ጋር ያለውን ችግር በውይይትና በሰላም ለመፍታት የተናጥል ተኩስ አቁም በማድረግ ለትግራይ ህዝብ ፈርጀ ብዙ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደርስ ማድረጉን አቶ ደመቀ አስታውቀዋል።

የህወሃት ቡድን የሰላም አማራጩን ወደ ጎን በማለት ለዳግም ጦርነት ቅስቀሳ ላይ መሆኑን ጠቅሰው መንግስት ችግሮችን በውይይትና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

የትግራይ ህዝብ መብቱንና ነፃነቱን ለማረጋገጥ የጋራ ጠላት የሆነውን የህወሃት ቡድን ጭቆና በቃ ሊለው እንደሚገባ ተናግረዋል።

የሰላምን ጥሪ በማይቀበሉና የሀገርን ሉዓላዊነት የሚፈታተኑ ቡድኖች እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ዛሬም በድል እንደሚመከቱ ገልጸዋል።

በአፋርና በአማራ ክልሎች በጦርነቱ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ የመገንባት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያረጋገጡት።

ኢትዮጵያዊያን ከትንንሽ አጀንዳዎች በመውጣት አንድነትን አጠናክሮ ማስቀጠል ላይ ማተኮር እንዳለባቸውም መልእክት አስተላልፈዋል።

አቶ ደመቀ የሻደይን በዓል በነፃነት እንዲከበር የሀገር መከላከያ ሰራዊትና የኢትዮጵያ ህዝብ ላበረከቱት ተጋድሎ ምስጋና አቅርበዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው የሻደይ በዓል የስልጣኔ ምልክት የሆነ ትልቅ ፀጋ ነው ብለዋል።

በኮሮና ቫይረስና በህወሃት ወረራ ምክንያት የሻደይ በዓል ባለፈው አመት ሳይከበር መቅረቱንም አስታውሰዋል።

"የትግራይ ህዝብ ወንድም የሆነ ህዝብና ለሀገር ግንባታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ይልቃል ፤በህወሃት የጥፋት ጥሪ ሳይወናበድ እንደቀደመ ታሪክ ሁሉ የጋራ ጠላት የሆነውን ቡድን ሊታገል ይገባል ነው ያሉት።

የሴቶች በተለይም የልጃገረዶች መገለጫ የሆነውን የሻደይ በዓል የቱሪዝም መስህብ እንዲሆን የክልሉ መንግስት ጠንክሮ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የአገው ህዝብ ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት መከበር የበኩሉን የተወጣ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ስቡህ ገበያው ናቸው።

"የዘንድሮው የሻደይ በዓል በድምቀት መከበር የሀገርን ሰላምና መተባበር የሚያጠናክር በመሆኑ የጠላትን ቅስም የሰበረ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

የሻደይ በዓል ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር አስተዳደሩ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም