ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደረገለት - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደረገለት
ነሐሴ 16 2014 (ኢዜአ) ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ እንዲሁም የኔዘርላንድስና የኦስትሪያ ቀይ መስቀል ማህበራት ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የአምቡላንስ እና መሰል የግብአት ድጋፍ አደረጉ።
ኮሚቴውና ማህበራቱ የ20 አምቡላንሶች፣19 ቀላል ተሽከርካሪዎች እና 25 ጄኔሬተሮች ድጋፍ ነው ያደረጉት።
ድጋፋ በዋናነት ግጭትና የተፈጥሮ አደጋ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ላሉ የጤና ተቋማት ተደራሽ የሚሆኑ ናቸው ተብሏል።
ይህም ችግሩ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ላሉና ሰብአዊ ድጋፍን ለሚሹ ወገኖች ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ያቃልላል ተብሎ ታምኖበታል።
የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ የኢትዮጵያ ልዑክ ኃላፊ ኒኮላስ ቮን አርክስ ድጋፉ በኢትዮጵያ በግጭትና በተፈጥሮ አደጋ ሳቢያ የሕክምና ቁሳቁስ እጥረት ያጋጠማቸውን የአገሪቱ አካባቢዎች ታሳቢ በማድረግ የተሰጠ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ዋና ፀሐፊ አቶ ጌታቸው ታዓ በበኩላቸው ድጋፉ በድርቅ እና በሌሎች ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እንዲሁም ጦርነቱ ተከስቶባቸው በነበሩ አካባቢዎች ላሉ የጤና ተቋማት ድጋፉ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
የተደረገው ድጋፍ በቅርቡ ለክልሎች እንደሚሰራጭም ጠቁመዋል።