ከቡራዩ፣ ከታና ሌሎች የኦሮሚያ ክልሎች የተፈናቀሉ ነዋሪዎች በአዲስ አበባ ህዝብ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከቡራዩ፣ ከታና ሌሎች የኦሮሚያ ክልሎች የተፈናቀሉ ነዋሪዎች በአዲስ አበባ ህዝብ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው
አዲስ አበባ መስከረም 7/2011 በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙት አካባቢዎች በደረሰው ጥቃት ሳቢያ በቡራዩ፣ ከታና ሌሎች አካባቢዎች ከቤታቸው ተፈናቅለው በአዲስ አበባ ጀኔራል ዊንጌት ቴክኖክና ሙያ ኮሌጅ ውስጥ ተጠልለው ለሚገኙ ተጎጂዎች የአካባቢው ህብረተሰብ ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑ ተገለጸ። ተፈናቃዮቹ የአልባሳት፣ የምግብና የመጠጥ እንዲሁም የህክምና ድጋፍ እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል። ከአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ክልል ቡራዩ፣ ከታ፣ አሸዋ ሜዳና ሌሎች አካባቢዎች ተፈናቅለው በኮሌጁ የተጠለሉትን የኢዜአ ሪፖርተሮች በቦታው ተገኝተው አነጋግረዋቸዋል። ተፈናቃዮቹ እንዳሉት፤ ዘረፋና የውንብድና ተግባር ተፈጽሞባቸው ለረጅም ዓመታት ከኖሩበት፣ ኃብትና ንብረት ካፈሩበት አካባቢ በህገ-ወጥ መንገድ በተደራጁ ቡድኖች በደረሰባቸው ጥቃት ተፈናቅለዋል። ከተፈናቃዮች መካከል ካፊታ ካታ«በድንጋጤ ብቻ አንጀታችን ታስሮ ዛሬ ነው ምግብ የቀመስነው፤ ከመስከረም አንድ ጀምሮ አንጀታችን ደርቆ ተጎድተናል ፤የኢትዮጵያ ህዝብ እግዚአብሄር ይስጠው ተባረኩ እርቦን አበላችሁን ጠምቶን አጠጣችሁን፤ እግዚአብሄር ይባርካችሁ »ሲሉ ተናግረዋል፡፡ "ባለቤቴ የአንድ ወር ከሃያ ቀን ህጻን ይዛ ነው እዚህ ያለችው ፤ገና ከአልጋ አልተነሳችም ለመናገር ቃላት ያጥረኛል፤ ፤ወጣቶች ላበረከቱት አስተዋጽኦ ክብርና ምስጋና ይድረሳችሁ "ያሉት ደግሞ አምሳ ተልቤ ናቸው ተፈናቃዮች ወደ መጠለያው እስከመጡበት ጊዜ ድረስ በርካታ ችግሮች እንዳሳለፉ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች ከነዚህ ቡድኖች ጥቃት ለመከላከል ጥረት ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ተፈናቃዮች ባረፉበት ጀኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ሲያስተባበር ያገኘነው በጎ ፈቃደኛ ወጣት ቴዎድሮስ ካሳሁን የአካባቢው ህብረተሰብ በተቻለው መጠን ብዙ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ገልጿል። ወጣት ቴዎድሮስ እንዳለው እነዚህ ተፈናቃዮችን ዛሬ የአካባቢው ህብረተሰብ ድጋፍ እያደረገላቸው ቢሆንም መንግስት ቋሚ በሆነ መንገድ ድጋፍ የሚያገኙበትን ሁኔታ ሊያመቻች ይገባል ብሏል። የኢዜአ ሪፖርተሮች ያነጋገሯቸው ተጎጂዎችም መንግስት አስቸኳይ እርዳታ እንዲያደረግላቸው ጠይቀዋል።