ቀጥታ፡

ክልሉ በተፈጠረው ግጭት በህይወትና በንብረት ላይ ለደረሰው ጉዳት የተሰማውን ሀዘን ገለፀ

መስከረም 8/2011 በቡራዩና አከባቢዋ በተፈጠረው ግጭት በህይወትና በንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማው የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ገለፀ። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ በቡራዩና አከባቢዋ የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ በደረሰው ጉዳት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማቸው ገልፀው  የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማቋቋም  ክልሉ ሙሉ ኃላፊነት ወስዶ ይሰራልም ብለዋል። በተሰራው ሥራም  እስከ አሁን 300 አባወራዎችን ወደ ቀያቸው መመለስ መቻሉንም  ገልፀዋል። በግጭቱ እጃቸው አለበት የተባሉ 200 ተጠርጣሪዎችና የተለያዩ የጦር መሳርያዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ነው ያብራሩት። ግጭቱን ወደተለያዩ አከባቢዎች በተለይ ወደ አሰላ አከባቢ ለማስፋፋት ቢሞከርም ህብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ባደረገው ትብብር መክሸፉንም ገልፀዋል። ህብረተሰቡ አሁንም በተረጋጋ ስሜትና በማስተዋል ሊንቀሳቀስ እንደሚገባም አሳስበዋል። በተለያዩ አከባቢዎች እየተንቀሳቀሱ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አክቲቪስቶች የሚያስተላልፉት መልዕክት ህዝቦችን የሚያቀራርብ ና ወደ አንድነት የሚያመጣ እንጂ የሚያለያይ ሊሆን እንደማይገባም አቶ ለማ ተናግረዋል። ለሚፈጠሩ ችግሮችም መንግስት በትዕግስት የሚያልፍበት ሁኔታ እንደማይኖርም ነው ያሳሰቡት። ከፌዴራልና ከኦሮሚያ ፖሊስ የተውጣጣ ግብረ ኃይል ተዋቅሮ ያሉትን ሁኔታዎች ለማርገብ እንዲሁም ወደፊት ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ለመከላከል እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም  አቶ ለማ ገልፀዋል። ምንጭ፡- OBN
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም