በደቡባዊ አፍሪካ የኢትዮጵያውያን ማህበር ከኢትዮጵያ የትምህርትና ምርምር ተቋማት ጋር ትስስር እንዲፈጠር ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
በደቡባዊ አፍሪካ የኢትዮጵያውያን ማህበር ከኢትዮጵያ የትምህርትና ምርምር ተቋማት ጋር ትስስር እንዲፈጠር ይሰራል
ነሐሴ 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) የደቡባዊ አፍሪካ የኢትዮጵያውያን ማህበር በኢትዮጵያ ከሚገኙ የትምህርትና ምርምር ተቋማት ጋር ትስስር እንዲፈጥር መስራቱን በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አመለከተ።
በደቡባዊ አፍሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዶክተር ሙክታር ከድር በደቡባዊ አፍሪካ የኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ማህበር የሥራ አስፈጻሚ አባላት ጋር የሥራ ትውውቅና ውይይት አካሂደዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ማህበሩ ከአሁን በፊት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታና ተያያዥ ጉዳዮች፣ ከህልውና ዘመቻ ጋር በተገናኘ ሲሰራጩ የነበሩ የሀሰት መረጃዎችን የማጋለጥ እና በሌሎችም አገራዊ ጉዳዮች ላይ ታዋቂ ምሁራንን ያሳተፈ ትላልቅ የውይይት መድረክ ማዘጋጀቱ ተገልጿል።
ማህበሩ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ድጋፎች ያደረገ ሲሆን የማህበሩ አባላት በኢትዮጵያ ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ትስስር ፈጥረው የዕውቀትና ልምድ ልውውጥ በማድረግ የአቅም ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ነው።
ማህበሩ በቀጣይ በይበልጥ እንዲጠናከርና የአባላቱን አቅም ተጠቅሞ በአገራዊ ግንባታ ሂደት አስተዋጽኦን እንዲያበረክት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁነት እንዳለ አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።
ማህበሩ በዋናነት በደቡባዊ አፍሪካ አገራት በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርትና ምርምር ተቋማት የሚገኙ ከፍተኛ የኢትዮጵያ ምሁራንን በአባልነት ያካተተ መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።