ቀጥታ፡

በነገው ዕለት ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋናው መስሪያ ቤት የሚወስዱ መንገዶች በስራ ምክንያት ለተሽከርካሪ ዝግ ይሆናሉ

ነሐሴ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) በነገው ዕለት ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋናው መስሪያ ቤት የሚወስዱ መንገዶች በስራ ምክንያት ለተሽከርካሪ ዝግ እንደሚሆኑ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ከተለያዩ አቅጣጫዎች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አምባሳደር አካባቢ አዲስ ወዳስገነባው ዋና መስሪያ ቤት ህንፃ የሚወስዱ መንገዶች በስራ ምክንያት ከለሊቱ 11 ሰዓት ጀምሮ ለተሽከርካሪ ዝግ እንደሚሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

በዚህም መሰረት ከሴንጆሴፍ መብራት ወደ ሃራምቤ ሆቴል፣ ከኢሚግሬሽን ወደ ፍልውሃ፣ ከፍል ውሃ ወደ ኢትዮጵያ ሆቴል፣ ከጤና ሚኒስቴር ወደ ፍልውሃ እና ከለገሃር ወደ ፍልውሃ የሚወስዱት መንገዶች ስራው እስኪጠናቀቅ ድረስ ለተሽከርካሪ ዝግ እንደሚሆኑ ተጠቁሟል።

በመሆኑም አሽከርካሪዎች የትራፊክ ፖሊስ አባላት በሚያመላክቷቸው አቅጣጫ መሰረት ሌሎች አማራጭ መንገዶችን በመጠቀም አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳስቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም