ነፃ የንግድ ቀጠናው ለሀገር ዘላቂ ዕድገት ያለውን አስተዋጽኦ በተግባር ማሳየት ጀምሯል-አቶ ሳንዶካን ደበበ - ኢዜአ አማርኛ
ነፃ የንግድ ቀጠናው ለሀገር ዘላቂ ዕድገት ያለውን አስተዋጽኦ በተግባር ማሳየት ጀምሯል-አቶ ሳንዶካን ደበበ
ድሬዳዋ፤ ነሐሴ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ለሀገር ዘላቂ ዕድገትና ለዜጎች ኑሮ መለወጥ ያለውን አስተዋጽኦ በተግባር ማሳየት መጀመሩን የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ አስታወቁ።
"ኤል አውቶ " ኢንጂነሪንግ እና ትሬዲንግ በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና በ400 ሚሊዮን ብር ያስገነባቸው የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ተመርቆ ዛሬ አገልግሎት ጀምሯል፡፡
አቶ ሳንዶካን በወቅቱ ባደረጉት ንግግር ፤ ነፃ የንግድ ቀጠናው ለሀገር ዘላቂ ዕድገትና ለዜጎች ኑሮ መሻሻል ያለውን አስተዋጽኦ በተግባር ማሳየት መጀመሩን ገልጸዋል።
ዛሬ ተመርቆ ሥራ የጀመረው የመኪና መገጣጠሚያ አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ ግዙፍ አምራች ኢንዱስትሪዎች በቀጠናው ገብተው ለሀገርና ለዜጎች ዕድገት መሠረታዊ ለውጥ እንዲያመጡ የተቀናጀ ድጋፍና ርብርብ ይደረጋል ብለዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው፤ የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ በየመስኩ የሚደረገው ድጋፍ ይጠናክራል ነው ያሉት።
የመገጣጠሚያ ፋብሪካው ለድሬዳዋ ዕድገትና ለዜጎች የሥራ ዕድል ማግኛ በመሆን ሁሉን አቀፍ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ያደረገላቸው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለኢንቨስትመንት ሥራ ምቹና ሳቢ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የ"ኤል አውቶ" ኢንጂነሪንግና ትሬዲንግ መስራችና ፕሬዚዳንት አቶ ቶኩቻ አለማየሁ ናቸው።
"ኤል አውቶ" በሀገር ውስጥና በውጭ በዘረጋቸው ቅርንጫፎቹ በመታገዝ የሀገርና ውጭ ገበያ ድርሻውን በማሳደግ የውጭ ምንዛሬ በማስቀረትና በማስገባት ለሀገር ዕድገት የድርሻውን ይወጣል ብለዋል፡፡
በዛሬ እለት ለምርቃት የበቃው አንደኛው ሼድ 400 ሚሊዮን ወጪ የተደረገበት ሲሆን 300 ሚሊዮን ወጪ የተደረገበት ሁለተኛው ሼድ በአንድ አመት ውስጥ ተጠናቆ ወደ ሰራ ይገባል ብለዋል።
ኤል አውቶ በቀን እስከ 35 መኪናዎች በመገጣጠም የሀገር ውስጥ የገበያ ድርሻውን እንደሚጋራ ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ቶኩቻ ገለፃ ፤ "ኤል አውቶ" የሀገር ሁሉን አቀፍ ዕድገት ብቻ ሣይሆን ለ300 ዜጎችና በተዘዋዋሪም በሺዎች ለሚቆጠሩ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡
በፋብሪካው የሥራ ዕድል ካገኙት መካከል ወጣት አዳም ማጀር በሰጠው አስተያየት ፤ይህ ትልቅ ተስፋ ነው፤ ከሥራ ዕድል በተጨማሪ ጥሩ የተግባር ዕውቀት እየቀሰምን በመሆኑ ተደስተናል ብሏል፡፡
ሌላኛው ወጣት ዳዊት ታደሰ በበኩሉ፤ ነፃ የንግድ ቀጠናው ለዜጎችና ለሀገር ሁለንተናዊ ለውጥ ወሳኝ ድርሻ እንደሚኖረው በተግባር ማሳየት መጀመሩን ገልጿል፡፡