ቀጥታ፡

የተቀናጀ ሙያዊ የብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ሰርተፊኬት መስጠት የሚያስችል መተግበሪያ በልፅጎ ስራ ላይ ይውላል

ነሐሴ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የተቀናጀ ሙያዊ የብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ሰርተፊኬት መስጠት የሚያስችል መተግበሪያ በልፅጎ ስራ ላይ ለማዋል የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ።

የስራና ክህሎት ሚንስቴርና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቲዩት የተቀናጀ መተግበሪያው በልጽጎ ስራ ላይ እንዲውል የሚያስችል የጋራ ስምምነት ተፈራርመዋል።

የመግባቢያ ስምምነቱን የስራና ክህሎት ሚንስትሯ ሙፈርያት ካሚል እና የኢንስቲቲዩቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ወርቁ ጋቸና ተፈራርመዋል።

የተለያዩ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሚያሰለጥኑትን የሰው ሃይል እውቅና የሚሰጥበት አዲስ የአሰራር ስርአት መዘርጋቱን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

ለዚህም ስምምነቱ ለሰልጣኞች የሚሰጠውን የእውቅና ስርአት ዲጂታላይዝ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

በስምምነቱ መሰረት አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቲዩት መተግበሪያውን በስድስት ወራት ውስጥ አልምቶ ወደ ስራ የሚገባ ይሆናል።

በመሆኑም ስራ ላይ የሚውለው ሲስተም ከእጅ ንክኪ ነጻ በመሆኑ የእውቅና ስርአቱ ከሙስና እና ከስርቆት የጸዳ እንዲሆን ያስችላል ብለዋል ሚኒስትሯ።

ከኢንስቲቲዩቱ ጋር በቀጣይ ሌሎች ስራዎችንም በትብብር ለማከናወን የታቀደ መሆኑን ጠቅሰው ስምምነት የተደረገበት ሲስተም በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገባ ይደረጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና፤ ኢንስቲቲዩቱ በዋናነት ተቋማት በቴክኖሎጂ እንዲዘምኑ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ተቋማት ሲስተማቸውን በማሳደግ ፈጣን እና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር የተደረገው ስምምነትም የዚሁ አንድ አካል ነው ብለዋል።

በስምምነቱ መሰረት የተቀናጀ ሙያዊ ብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ሲስተም መተግበሪያ በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ለምቶ ስራ ላይ ይውላል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም