የኢትዮጵያን የዓሳ ሃብት ልማት የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው- የግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የዓሳ ሃብት ልማት የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው- የግብርና ሚኒስቴር
ነሐሴ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን የዓሳ ሃብት ልማት የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
የሁሉ መገኛ (LAND OF ORIGINS) በመባል የምትታወቀው ኢትዮጵያ የአየር ንብረቷ ለሰው ልጆች ኑሮ የሚስማማ፣ ለእንስሳትና እጽዋት ልማትም በእጅጉ ተመራጭ መሆኑ ይነገርላታል።
ኢትዮጵያ ከራስ ደጀን ተራራ እስከ ሞቃታማው ዳሎል ድረስ የማይነጥፍ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት የሆነች ድንቅ አገር መሆኗንም ያዩ ሁሉ የሚመሰክሩት ሃቅ ነው።
በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙት ሃይቆቿም ጨዋማነት የሌላቸው ተጨልፎ የሚጠጣ ውሃ እና በርካታ የዓሳ ዝርያዎች የሚረቡባቸው መሆናቸው ይነገራል።
እነዚህ ሁሉ ተዝቀው የማያልቁ ሃብቶች እያሉ ግን ለአገራዊ የኢኮኖሚ ልማት ለማዋልና ለህዝብ ተጠቃሚነት እስካሁን በአግባቡ አልዋሉም።
በተለይም የኢትዮጵያ የዓሳ ሃብት የመልማት አቅምና ጥቅም ላይ የማዋል እንቅስቃሴ ተዳክሞ የቆየ በመሆኑ በአስር አመቱ ስትራቴጅክ የልማት እቅድ ልዩ ትኩረት ሰጥቶታል።
በግብርና ሚኒስቴር የዓሳ ሃብት ልማት ባለሙያው በቀለ የኋላሸት የዘርፉን ልማት የአገር የእድገት አማራጭ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት እየተከወኑ መሆኑን ይናገራሉ።
እስካሁን ባለው ሂደት በአመት እስከ 73 ሺህ ቶን ዓሳ እንደሚመረት ጠቅሰው፣ ካለው ፍላጎት አንጻር ምርቱ በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
የዘርፉን አመራረት ዘመናዊ አለማድረግ፣ የመሰረተ ልማት መጓደልና ለዘርፉ ልማት የተሰጠው ትኩረት ማነስ ለምርቱ ማነስ ከሚጠቀሱት ምክንያቶች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በእቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት ባለሙያው በ2015 በጀት አመት 106 ሺህ ቶን ዓሳ ለማምረት የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የግል ባለሃብቶች በዘርፉ በስፋት እንዲሰማሩና በዓሳ ሃብት ምርምር ላይ ከሚሰሩ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች ተቋማትም ጋር በቅንጅት እየተሰራ ስለመሆኑ አንስተዋል።
የዘርፉ ማነቆ የነበሩ ችግሮችን በማስወገድ አሰራሩን ለማዘመን የቴክኖሎጅ ግብዓቶች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ የማድረግ ስራም ተጀምሯል ብለዋል።
የዓሳ ሃብት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከማገዝ ባለፈ በወስጡ "ኦሜጋ ስሪ ፋቲ አሲድ" የተባለ ንጥረ ነገር ስላለው ለማህበረሰብ ጤና የላቀ ጥቅም እንዳለው አብራርተዋል።
በስትራቴጅክ እቅዱ የዓሳ ግብርና (አኳ ካልቸር) ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ተደርጎ መያዙን ጠቅሰዋል።
በዓሳ ሃብት ልማት ዙሪያ የምርጥ-ዘር ማስፋፊያ ማዕከላትን የማቋቋምና አስጋሪዎችም በህጋዊና ዘመናዊ መንገድ እንዲሰሩ የአቅም ግንባታ ስራዎች በስፋት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።