በጅማ ከ7ሺህ 500 በላይ ህገ ወጥ ሲም ካርድ የተገኘበት ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

119

ጅማ፣ ነሀሴ 13/2014(ኢዜአ) በጅማ ከተማ ከ7ሺህ 500 በላይ ህገ ወጥ ሲም ካርድ የተገኘበት ተጠርጣሪ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።

በጅማ ከተማ የወረዳ ሁለት ፖሊስ ጽህፈት ቤት አዛዥ ኮማንደር ጌታሁን ከበደ ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማው ጊንጆ ቀበሌ ነዋሪ የሆነ ግለሰብ  በመኖሪያ ቤቱ ካከማቸው ህገወጥ ሲም ካርድና ሌሎች ቁሶች ጋር በቁጥጥር ስር ውሏል።

ግለሰቡ ሞተር ሳይክል ሲጓዝ በተደረገበት ድንገተኛ ፍተሻ በእጁ የተገኘን 300 ሲም ካርድ መሰረት በማድረግ  ትናንት ነሀሴ 12 ቀን 2014 ዓም ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ላይ በመኖሪያ ቤቱ በተደረገ ፍተሻ  ተጨማሪ 7 ሺህ 277 ሲም ካርዶች መገኘታቸውን ተናግረዋል ።

ከሲም ካርዱ  በተጨማሪ አንድ ሀሰተኛ ማህተም፣ 12 ባዶ መታወቂያ ደብተር፣ አንድ የልደት ሰርተፍኬት በፍተሻው የተገኘበት መሆኑን አመልክተዋል።

ፖሊስ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ኮማንደር ጌታሁን ከበደ አስታውቀዋል።

በጅማ ከተማ ከዘጠኝ ወር በፊት ከ9ሺህ በላይ ህገ ወጥ ሲም ካርድ በቁጥጥር ስር መዋሉን ኢዜአ መዘገቡ  ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም