ዘላቂነት ያለው የድንበር ተሻጋሪ ትብብር እውን እንዲሆን ሁሉም የናይል አባል ሀገራት የሚተዳደሩበት ህጋዊ ማእቀፍ ያስፈልጋል - ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ

57

ነሐሴ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዘላቂነት ያለው የድንበር ተሻጋሪ ትብብር እውን እንዲሆን ሁሉም የናይል አባል ሀገራት የሚተዳደሩበትና የሚገዙበት ህጋዊ ማእቀፍ እንደሚያስፈልግ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ አመለከቱ።

30ኛው የናይል ሀገራት የሚኒስትሮች ካውንስል ጉባኤ በታንዛንያ እየተካሄደ ነው

በጉባኤው ላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የተፋሰሱ ሀገራት ትብብር  በጠንካራ ህጋዊ መሰረት ላይ ለማንበር የጋራ ጥረት ተደርጓል።

በዚህም አራት የናይል ቤዝን ኢንሼቲቭን (NBI) አባል ሀገራት የትብብር ማዕቀፉን (CFA) እንደ ብሔራዊ ህግ ማጽደቃቸውን ገልጸዋል።

የትብብር ማእቀፉን ያፀደቁ ሀገራትን ቁጥር ለማሳደግ የናይል ቤዝን ኢንሼቲቭን (NBI) ወደታለመለት የኮሚሽን ደረጃ እንዲሸጋገር መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የትብብር ማዕቀፉን የማጽደቅ ሂደት ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንዳልሆነ የገለጹት ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ፤ ናይል ቤዚን ኢኒሽቲቭ (NBI) እንደ መሸጋገሪያ ማእቀፍ ሊያከናናቸው የማይችላቸው ስትራቴጂያዊ እና ሽግግራዊ ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በመሆኑም የናይል ተፋሰስ ልማት እና አስተዳደር ጉዳዮች ለማሳካት የትብብር ማእቀፉ መጽደቅ መሰረታዊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው አስረድተው፤ ሁሉም አባል ሀገራት ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ መሆን እንዳለበትም መግለጻቸውን ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለኢዜአ የላከው መግለጫ ያመለክታል።

የናይል ተፋሰስ ኢኒሸቲቭ (NBI) የሽግግር ማእቀፍ ሆኖ በዘጠኝ መስራች አባል ሀገራት የጋራ ራእይ የተመሰረተና ቋሚ የናይል ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን እስከሚመሰረት የሽሽግር ማእቀፍ ሆኖ እንዲያገልገል ታስቦ መቋቋሙ ይታወቃል።

ከ30ኛው የናይል ሀገራት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጉባኤ ጎን ለጎን 25ተኛው የናይል ኢኳቶሪያል ሀይቆች ካውንስል ጉባኤ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

34ተኛው የምስራቅ ናይል ተፋሰስ ሀገራት ሚኒስትሮች ካውንስል ጉባኤ ትናንት መካሄዱ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም