ለማዕከሉ ከአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር 20ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ተበረከተ

142

አርባ ምንጭ (ኢዜአ) ነሐሴ 13/2014 የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ለመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል 20 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ በነፃ አበረከተ።

አስተዳደሩ ቦታውን ዛሬ ያስረከበው በከተማው ለሚገነባው የአረጋውያንና አዕምሮ ሕሙማን ማዕከል ማስሪያ እንዲሆን ነው።

የቦታ ርክክቡን ተከትሎ ለማዕከሉ ግንባታ እንዲሆን የመሠረት ድንጋይ የተጣለ ሲሆን ለግንባታ ማስጀመሪያም ከተማ አስተዳደሩ 1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።

የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ማርቆስ ማቴዎስ በእዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ በአንድ ወቅት ገናና የነበሩ፣ የሰውን ችግር የፈቱና የተማሩ ሰዎች ጭምር በተለያዩ ምክንያቶች የወገንን ድጋፍ የሚሹበት ሁኔታ ይከሰታል።

እንደ መቄዶንያ ያሉ በጎአድራጊዎች አረጋዊያንና የአዕምሮ ሕሙማንን ከወደቁበት እየታደጉ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ማዕከሉ ሥራውን በተሻለ እንዲያከናውን የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ለመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል 20 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ዛሬ ማበርከቱን ገልጸዋል።  

"ለማዕከሉ ግንባታ ማስጀመሪያም 1 ሚሊዮን ብር በማበርከት ማህበራዊ ኃላፊነቱን ተወጥቷል" ሲሉም ከንቲባው አክለዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ከተለያዩ በጎ አድራጎት ማህበራት ጋር አብሮ እየሰራ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ማርቆስ፣ "ማዕከሉ ተገንብቶ እስኪጠናቀቅ ድረስም ህብረተሰቡን በማስተባበር ተጨማሪ ድጋፍ ያደርጋል" ብለዋል

በመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል የክልል ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አቶ ማህተመ በቃሉ በበኩላቸው፣ በአሁኑ ወቅት ከ7ሺህ 500 በላይ አረጋውያንና አዕምሮ ሕሙማንን ማዕከሉ ከወደቁበት አንስቶ እየታደገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ችግር፣ ረሀብ እና ስቃይ ጊዜና ፋታ ስለማይሰጡ ለችግር የተዳረጉ ኢትዮጵያዊያንን ለመታደግ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

እንደ አቶ ማህተመ ገለጻ ማዕከሉ በስድስት የክልል ከተሞች ቅርንጫፍ ከፍቶ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን ወገኖች እየደገፈ ይገኛል።

"በተያዘው በጀት ዓመትም በ14 የክልል ከተሞች ተጨማሪ ቅርንጫፎችን ለመክፈትና ለችግር የተዳረጉ ወገኖችን ይበልጥ ተደራሽ ለመሆን እቅድ ይዞ እየሰራ ይገኛል" ብለዋል።

ማዕከሉ በዛሬው እለትም 37 አረጋውያንን ከአርባ ምንጭ ከተማ መረከቡን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

በጋሞ ዞን ገረሰ ወረዳ ከ7 ዓመት በፊት በደረሰባቸው የተሸከርካሪ አደጋ ኩላሊታቸው ተጎድቶ ሁለት ዓመት ሙሉ የአልጋ ቁረኛ እንደነበሩ ያስታወሱት ደግሞ በማዕከሉ ድጋፍ የተደረገላቸውና የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪው የሆኑት አቶ ሀዋሳ አንጁሎ ናቸው።

ማዕከሉ 150 ሺህ ብር የሕክምና ወጪያቸውን በመሸፈኑ ባደረገላቸው ድጋፍ በአሁኑ ወቅት ጤናቸው ወደ ቀድሞ ሁኔታው መመለሱን አስረድተዋል።

"ነገ በማናችንም ላይ የሚሆነውን ነገር አናውቅም" ያሉት አቶ ሀዋሳ፣ የመቄዶንያ አገልግሎት ለችግር የተዳረጉ ኢትዮጵያዊያን በስፋት ተደራሽ እንዲሆን ሁሉም የአቅሙን እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም