የደብረ ታቦር በዓል''ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር ከተማ'' በሚል መሪ ዐሳብ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ እየተከበረ ነው

203

ደብረ ታቦር ነሐሴ 13 ቀን 2014(ኢዜአ) የደብረ ታቦር በዓል '' ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር ከተማ'' በሚል መሪ ዐሳብ ሃይማኖታዊ ባህላዊ ክዋኔውን በጠበቀ መልኩ እየተከበረ ይገኛል።

በበዓሉ አከባበር መርሐግብር ላይ የፌደራልና የክልል አመራሮች ተገኝተዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ይርጋ ሲሳይ በዚህ ወቅት "የደብረ ታቦር በአልን በደብረ ታቦር ከተማ ስናከብር የአካባቢውን ታሪካዊና ባህላዊ ትውፊቶችን በማስተዋወቅ ለአገር ውስጥና ውጭ ጎብኞች ክፍት ለማድረግ ነው ብለዋል።

በዓሉ የአካባቢው የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን ለማድረግ የሚያግዙ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተደረገ ጠንካራ እንቅስቃሴ የደብረታቦር በዓል በደብረ ታቦር አከባበሩ እየደመቀ መምጣቱንና ቀጣይም የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

''የደቡብ ጎንደር ዞን ህዝብ አንድነቱን በማስጠበቅ ከመንግስት ጎን በመቆም ታሪክ መስራቱን ሊያስቀጥል ይገባል'' ያሉት ደግሞ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ናቸው።

"በዓሉ አገር ለማፍረስ የመጣውን አሸባሪው ህውሃት አከርካሪውን ተመቶ የተመለሰበት ቦታና ቀን በመሆኑ በአሉን ድርብ በአል ያደርገዋል" ብለዋል።አሸባሪ ቡድኑን በመደምሰስ በተካሄደው ትግል የዞኑ ህዝብ የአካል፣ የንብረትና የህይወት መስዋእትነት መክፈሉን ጠቅሰው፤ ይህንኑ ተጋድሎ በልማት ላይ መድገምና ድህነትን ማሸነፍ ይገባል ሲሉ ገልፀዋል።

አሁንም የዞኑ ህዝብ ወራሪው ሃይል እስካልጠፋ ድረስ ትጥቁን በማጥበቅና አንድነቱን በማጠናከር አገር ለማፅናት ከመንግስት ጎን እንዲቆም አሳስበዋል።

ለዚህም ባንድ እጁ ጦርና ጋሻ በሌላው እጅ ልማትን የሚያቀላጥፍ ህዝብ መሆን እንዳልበት ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

በበዓሉ አከባበር ላይ ህፃናት፣ ወጣቶችና ሴቶች የሆያ ሆየ፣ የአሸንድየና ሌሎች በአሉን የሚያስታውሱ ዝግጅቶች እያቀረቡነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም