በጉጂ ዞን አባያ ወረዳ ለአካል ጉዳተኛ ህጻናትና ሴቶች የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደረገ

189

ነሐሴ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ)በምዕራብ ጉጂ ዞን አባያ ወረዳ ለ43 አካል ጉዳተኛ ህጻናትና ሴቶች ከ700 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የተለያዩ ቁሶች ድጋፍ ተደረገ።

ድጋፉ የተደረገው አማኑኤል የአካል ጉዳተኞች የድጋፍ ቁሳቁሶች ማምረቻና ተራዲኦ ማህበር ከወርልድ ቪዥን ጋር በመተባበር እንደሆነ በርክክቡ ሥነ-ሥርዓት ወቅት ተገልጿል።

የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ መለስ ኢዮብ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት፤ ማህበሩ የተለያዩ የድጋፍ ቁሶችን በማምረት ለበርካታ አካል ጉዳተኞች በማመቻቸት ችግራቸውን ለማቃለል ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

ከወርልድ ቪዥን ጋር በመተባበርም በአባያ ወረዳ ለ43 ህጻናትና ሴቶች ባለሁለትና ሶስት እግር ዊልቸር፣ ከክራንችና መቆሚያ ዛሬ ደጋፍ ማመቻቸት መቻሉን አስረድተዋል።

ድጋፉ ከ700 ሺህ ብር በላይ ግምት እንዳለውና በተለይ ህጻናቱ ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

በርካታ ህጻናት በአካል ጉዳት ምክንያት ለችግር ተጋልጠው በቤት እንደሚገኙ ጠቁመው፤የህጻናቱን ችግር ለማቃለል ሁሉም ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ድጋፉ በጤና እክልና በተደራራቢ የአካል ጉዳት ከማህበረሰቡ የተገለሉ ህጻናትን ተደራሽ ያደረገ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በወርድ ቪዥን የአባያ አከባቢ ልማት ፕሮግራም የህጻናት ጥቃት መከላከልና ተሳትፎ ባለሙያ አቶ ሰለሞን ደምሴ ናቸው።

በወረዳው በተፈጥሮና ሰው ስራሽ ችግር ለአካል ጉዳት የተዳረጉ ህጻናት ከማህበራዊ ተሳትፎ እንዳይገለሉ ግንዛቤ መፍጠርን ጨምሮ እገዛ እየተደረገላቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

የአባያ ወረዳ ሴቶችና ህጻናት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ናናቲ ፍቃዱ በበኩላቸው፤ ጽህፈት ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ቤት ለቤት ባደረገው አሰሳ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ 542 ህጻናት በተለያዩ የአካል ጉዳት ሳቢያ በቤት እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

ህጻናቱንም ከቤት በማውጣት ከማህበረሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ ከማድረግ ባለፈ ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ እገዛ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

የዛሬውም ድጋፍ የዚሁ ጥረት አካላት መሆኑን ጠቅሰው በወረዳው የልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤት ለመክፈት ግንባታ መጀመሩንም ጠቁመዋል።

ልጁ ከ5 ወሯ ጀምሮ በእግሯና እጇ ላይ በተፈጠረ ጉዳት ለመቀሳቀሰ ተቸግራ ማደጓን የተናገሩት ደግሞ ድጋፍ ከተደረገላቸው ህጻናት መካከል የብልሴ ግርማ አባት አቶ ግርማ መንግስቱ ናቸው።

ብልሴ 8 ዓመት የሞላት ቢሆንም በአካል ጉዳት ሳብያ ዛሬም ወደ ትምህርት ቤት አለመሄዷ እንደሚያስቆጨው ጠቅሰዋል።ይሁንና ዛሬ የውልቸርና መቆሚያ ድጋፍ በመገኝቱ በቀጣይ ትምህርት ቤት ለመላክ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው ስለድጋፉ ምስጋና አቅርበዋል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭ ወይዘሮ አስቴር በርሶ በበኩላቸው በሁለቱ እግሯቿ ላይ ከልጅነት ጀምሮ በተፈጠረ ጉዳት ለመንቀሳቀሰ መቸገሯን ተናግራለች።

ዛሬ የሶስት እግር ውልቸር በማግኝቷ ደስተኛ መሆናቸውን ጠቅሰው በቀጣይ ተንቀሳቅሳ በመስራት እራሷንና ቤተሰቧን ለመደጎም ጥረት እንደምታደርግ ተናግራለች።

ድጋፉ ህጻናት ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ እገዛ ያለው ሲሆን አማኑኤል የአካል ጉዳተኞች የድጋፍ ቁሳቁሶች ማምረቻና ተራዲኦ ማህበር ከወርልድ ቪዥን ጋር በመተባበር ያሳናዳው መሆኑም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም