የአረንጓዴ አሻራ ልማት የተፋሰሶችን ህልውና የመታደግ ድርሻው ከፍተኛ በመሆኑ ሊጠናከር ይገባል

40

ነሐሴ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ)በኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ልማት የተፋሰሶችን ህልውና ለመታደግ ጉልህ ድርሻ ያለው በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ አስታወቁ፡፡

ዩኒቨርሲቲው የአባያና ጫሞ ሀይቆችን ከደለል ለመታደግ በአርባምንጭ ሰንሰለታማ ተራሮች ላይ ቦታ ተረክቦ የችግኝ ተከላ እያካሄደ መሆኑ ተመላክቷል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አመራሮችና ሠራተኞች በዛሬው ዕለት ከ13 ሺህ በላይ ችግኞችን በጫሞ ሀይቅ ተፋሰስ ተከላ አካሂደዋል፡፡

በመርሃ-ግብሩ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ እንዳሉት በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው የአረንጓዴ አሻራ ልማት የአባይ ወንዝን ጨምሮ የተፋሰሶችን ህልውና በመታደግ እንዲሁም የአየር ንብረት ብክለትን ለመከላከል ጉልህ አስተዋጾ አለው ፡፡

በተለይ እየገጠመ ያለው የአለም አቀፍ አየር ንብረት ለውጥና አደጋዎችን ለመመከት ተፋሰሶችን የማልማትና መልሰው እንዲያገግሙ የማድረግ ስራ ትኩረት የሚሻው መሆኑን አመልክተዋል።

በአገሪቱ 12 ትላልቅ ተፋሰሶች መኖራቸውን ጠቅሰው አብዛኞቹ ድንበር ተሻጋሪ በመሆናቸው ይዘው የሚሄዱትን ለም አፈር በማስቀረቱ ረገድ የአረንጓዴ ልማት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

"በብዙ ቢሊየን ብር እየተገነባ ያለው የህዳሴው ግድብ በደለል እንዳይጎዳ እንደ አይናችን ብሌን በመጠበቅና በመንከባከብ የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል" ሲሉም አስገንዝበዋል ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በስምንት ጣቢያዎች በሚዘጋጁ ችግኞች በመታገዝ የአባያና ጫሞ ሀይቆችን ከደለል ለመታደግ የአርባ ምንጭ ከተማ ሰንሰለታማ ተራሮችን ለማልማት የበኩሉን እንደሚወጣ አመላክተዋል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ እስካሁን የተተከሉ ችግኞች የጽድቀት መጠን ከ90 በመቶ በላይ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ ለመጪዉ ትዉልድ የለማች አገር ለማስረከብ ከምንም በላይ የአረንጓዴ አሻራ ልማትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአራት ዙር የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብር ከ75 ሺህ በላይ ችግኞችን በመትከል እንክብካቤ እያደረገ እንደምገኝ የተናገሩት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክተር ዶክተር ተክሉ ወጋየሁ ናቸዉ፡፡

ዩኒቨረሲቲው ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት ሲል ከ1 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ለአካባቢው ማህበረሰብ ማሰራጨቱን ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲዉ ስር በተለያዩ ወረዳዎችና ዞኖች ስምንት ችግኝ ጣቢያዎች እንደሚገኙ ጠቅሰዉ ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ በተሰጠዉ ትኩረት በየዓመቱ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ በጀት መድቦ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

"ለመጪዉ ትዉልድ ችግርን ሳይሆን ችግኝ በመትከል የለማች አገርን ማስረከብ ይጠበቅብናል" ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ በድሩ ህሪጎ ናቸው።

"በአሁኑ ሰዓት የህዝብ ቁጥር እየጨመረ ከመምጣቱም በላይ የኢንዱስትሪዉ አብዮት በአየር ንብረት ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ በመሆኑ ከተፈጥሮ ሀብቶች የምናገኘዉን ጥቅም ለማሳደግ ተፈጥሮን መንከባከብ አለብን" ብለዋል፡፡

በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት ዛሬ ከተተከሉት የደንና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ካላቸው ከ13 ሺህ በላይ ችግኞች መካከል ወይቤታ፣ ወይራ፣ ኮሪ፣የህንድ ዛፍ፣ቡና፣አፕል፣ማንጎ፣አቦካዶ፣ፓፓያና የእንስሳት መኖ እንደሚገኙበት ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም