ረቂቅ አዋጁ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ለአገሪቱ ልማት የሚኖራቸውን ሚና ለማጎልብት የሚያስችል መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ረቂቅ አዋጁ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ለአገሪቱ ልማት የሚኖራቸውን ሚና ለማጎልብት የሚያስችል መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ መስከረም 7/2011 የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ረቂቅ አዋጅ ከውጭ አገራት በሚገኘው የገቢ ምንጭ ላይ ያስቀመጠውን ክልከላ የሚያነሳና የምዝገባ ሥርዓቱ ግልጽና ቀላል በሆነ መንገድ እንዲመራ የሚያስችል መሆኑ ተገለጸ። ከዚህ በተጨማሪ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ለአገሪቱ ልማት የሚኖራቸውን ሚናንም ለማጎልበት የሚያስችል ነው ተብሏል። የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሄራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ህግ ማሻሻያ ላይ ከአባላቱ ጋር ዛሬ ውይይት አካሄዷል። የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶችን የተመለከተውን ረቂቅ አዋጅ ለማሻሻል በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽህፈት ቤት ስር የሲቪክ ማህበራት ህግ ንዑስ ኮሚቴ ተቋቁሟል። የኮሚቴው አባል አቶ ቁምላቸው ዳኜ በመድረኩ እንደገለጹት "የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ተግዳሮቶችን በማጥናት ለተለዩ ችግሮች መፍትሄ መስጠት የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቷል"። ረቂቅ አዋጁ የተጠቃሚዎችን መብት፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶችን የውስጥ አስተዳደር ነጻነትና ተጠያቂነት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ አግባብነት ካላቸው ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ጋር በተጣጣመ መልኩ የተዘጋጀ ነው ብለዋል። በአሁኑ ወቅት ስራ ላይ ባለው አዋጅ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ማህበራት ኤጀንሲ መሰረታቸው በአገር ውስጥ የሆነ በጎ አድራጎት ድርጅቶች እና የውጭ አገር በጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከል ልዩነት የሚፈጥር ሆኖ ይህም በውጭዎቹ በተላለፈው ውሳኔ ላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ የማቅረብና ፍትህ የማግኘት መብትን የሚከለክል መሆኑን አንስተዋል። ይኸውም በህገ መንግስቱ የተሰጠውን የአገሪቱ የመደራጀትና ህገ መንግስታዊ መብትን የሚጻረር መሆኑም ተገልጸዋል። ለበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ የተሰጠው ስልጣን ከፍተኛ የሆነና ቁጥጥርና ቅጣት ላይ ብቻ ያተኮረ እንደነበርም ተጠቅሷል። በመሆኑም አዋጁ የመደራጀት መብትን ከማስጠበቅና ለሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች እንቅስቃሴ የተመቻቸ ሁኔታ ከመፍጠር አንፃር፣ ለሁሉም ድርጅቶችና ማህበራት ፍትሃዊ በማድረግ የማሻሻያ ሀሳብ ተካቷል ነው ያሉት። ረቂቅ አዋጁ "መደገፍና ማበረታት ላይ ያተኮረና ድርጅቶች ራሳቸውን መቆጣጠር የሚችሉበት ስርዓት" ማካተቱንም አንስተዋል። ከውጭ አገራት በሚገኘው የገቢ ምንጭ ላይ ያስቀመጠውን ክልከላንም የሚያነሳና የምዝገባ ሥርዓቱ ግልጽና ቀላል በሆነ መንገድ እንዲመራ የሚያስችል መሆኑንም አክለዋል። የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሄራዊ ማህበራት ፌደሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት ስራ ላይ ያለው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጅ ፌዴሬሽኑ ስራዎቹን በአግባቡ ለማከናወን የሚያስችለው አልነበረም። ለአብነትም አካል ጉዳተኞች ላይ ለመስራት የተደራጁ ማህበራት ለስራ ማሰኬጃ የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ከ10 በመቶ በላይ የሚሆነው በውጭ አገራት ድጋፍ ላይ የተመሰረተ እንዳይሆን የሚከለክል ሲሆን ይህም ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር አስቸጋሪ መሆኑን አንስተዋል። በአገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ የፌዴሬሽኑ መዋቅሮች ወጥነት በጎደለውና በተበታታነ መልኩ ስራቸውን እንዲያከናውኑ ማድረጉንም ገልጸዋል። በመሆኑም በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚሰሩ ስራዎች ላይ የሚፈለገውን ውጤት ለማግኘት እንዳልተቻለ ነው የተናገሩት። አዋጁ ላይ የህግ ማሻሻያ መደረጉ በተለይም ለአካል ጉዳተኞች ብሩህ ተሰፋ የሚፈጥር አጋጣሚ መሆኑንም ገልጸዋል። በውይይቱ ላይ የተገኙ ባለ ድርሻ አካላት እንደተናገሩትም አዋጁ ከበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ዓላማ፣ ተልዕኮ እና ሁኔታ አንፃር ውጤታማ እና ገንቢ በሆነ መልኩ ሊሻሻል ይገባል ሲሉም ተናግረዋል፡፡