በአዲስ አበባ እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶች ለወጣቶች ተስፋን የሚሰጡ እና የሚያኮሩ ናቸው

110

ነሐሴ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ)በአዲስ አበባ ከተማ እየተገነቡ ያሉ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ለወጣቶች ተስፋን የሚሰጡ እና የሚያኮሩ ስራዎች መሆናቸውን ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመጡ ወጣቶች ተናገሩ፡፡

የአብረሆት ቤተ መጽሀፍት፣የወዳጅነት ፓርክ ምዕራፍ አንድና ሁለት፣ የስነጥበብና የሳይንስ ሙዚየም፣ የቤተ መንግስት መኪና ማቆሚያ እና አንድነት ፓርክ በወጣቶቹ ተጎብኝተዋል።

ጉብኝቱ "የኛ ዘመን ወጣት ሚና" በሚል ርዕስ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲከናወን የቆየው የተጽዕኖ ፈጣሪ ወጣቶች የውይይት ማጠቃለያ መሆኑ ተገልጿል።

ወጣቶቹ እንደሚሉት የፕሮጀክቶቹ አፈጻጸም ጠንካራ የስራ ባህልን ማዳበር ከተቻለ በአጭር ጊዜ ብዙ ለውጥ ማዬት እንደሚቻል ያመላከቱ ናቸው።

ወጣት ሎምቤቦ ሰለሞን እና አባንግ ኩምዳን ፕሮጀክቶቹ ኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ እንዳላት አመላካች ነው ብለዋል።አገር ተረካቢ ወጣቶች ከዚህ የተሻሉ ስራዎችን ለማከናወን ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ መሰረት የጣለ መሆኑንም ገልጸዋል።

ፕሮጀክቶቹ ከውበት እና ልማት ባለፈ ለወጣቶች በርካታ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ መሆናቸውን በመጥቀስ።ወጣት ፍጹም ግረፌ እና ወጣት አብርሀም ታደሰ በበኩላቸው ፕሮጀክቶቹ በአጭር ጊዜ ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚቻል አመላካች ናቸው ብለዋል።

''የፕሮጀክቶቹ በአጭር ጊዜ እውን መሆን የስራ ባህልን ማሳደግ እና ማዳበር እንደሚገባን አስተምሮናል''ያሉት ወጣቶቹ ያዩት ነገር ከፍተኛ የስራ ተነሳሽነት እንደፈጠረላቸው ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ የፕሮጀክቶቹ ግንባታ ለትውልድ የሚተላለፍ ቅርስ የተተወበት መሆኑን ወጣት ሯች ጎች እና ወጣት ደጉ ወዳጄ ገልጸዋል።''ፕሮጀክቶቹ መለወጥ እና ወደ ተሻለ ምዕራፍ መሻገር እንደሚቻል የተመለከትንበት ነው'' ሲሉ ወጣቶቹ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም